የኦህዴድ ሰዎች ፖለቲካዊ ሰምና ወርቅ   (ባዩህ ተስፋየ)

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

እንደሚታወቀው የኦህዴድ ሰዎች የስልጣን መንበሩን ለመያዝ ማኮብኮብ ከጀመሩበት አንስቶ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ የሚለውን ስም በስብከት ደረጃ አንድ ሽህ አንድ ጊዜ ጠርተዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም። እነዚህ የኦህዴድ ሰዎች ከጅምሩ አንስቶ ኢትዮጵያ ሱሴ ነች፣ ከኢትዮጵያዊነት ውጭ መኖር አይቻልም፣ እማማ ኢትዮጵያ ብትጎብጭም አልተሰበርሽም፣ ብትመነምኝም አልተበጠስሽም በሚሉ ባማሩና በተከሸኑ ቃላቶች እንዲሁም አረፍተ ነገሮች ለትዮጵያ ያላቸውን “ወደር የሌለው ፍቅር” ሲገልፁ ሰምተናል። ዶ/ር አብይም በየክልሉ እየዞሩ ሲሰብኩ የነበሩት ይህንኑ ነው። አሁንም በስብከት ደረጃ ኢትዮጵያ የሚለው ስም ካፋቸው አይጠፋም።

በዚህም ምክንያት ህዝቡ ከዳር እስከዳር በሚባል ሁኔታ ድጋፉን አሳይቷቸውል። በተለይ የመገናኛ ብዙሃኑን የተቆጣጠሩት ልሂቃን ዶ/ር አብይና ሌሎች የኦህዴድ ሰዎች የሚናገሯቸውን የኢትዮጵያዊነት ስሜት የሚኮረኩሩ ንግግሮች በማስተጋባት የነዚህ የኦህዴድ ሰዎች ዝና እንዲገንና እንዲናኝ ከፍተኛውን ሚና ተጫውተዋል። በጣም በተለየ ሁኔታ ደግሞ የአማራው ልሂቃን በስብከቶቹ ምክንያት ለዶ/ር አብይና ለአቶ ለማ እንደቀጤማ ተጎዝጉዘውላቸዋል፤ ጫማ ለመሳምና በአራት እግራቸው ለመሄድም ተገልግለዋል። ይህንኑ የሚገልፀውን ደስታቸውንም ለአለም ሁሉ አሰራጭተዋል።

አሁን አሁን ግን ዶ/ር አብይ በተለይም ደግሞ እነ አቶ ለማ እየሄዱበት ያለው አቅጣጫ የሚያምር አይነት ስላልሆነ እንዴት ነው ነገሩ የሚል ሰው እየበዛ መጥቷል። ለዚህ ጥያቄ መነሻ የሆነውም የሚሰበከውና በተግባር የሚታየው ነገር አራምባና ቆቦ እየሆነ በመምጣቱ ነው። ስብከቱ (ሰሙ ለማለት ነው) በዚህ ፅሁፍ ከፍ ብሎ እንደተገለፀው በኢትዮጵያዊነት ስም የተጀቦነ ማማለያ ነው።  ተግባሩ (ወርቁ) ደግሞ ኦሮሟዊነት እየሆነ ነው። በሌላ አነጋገር ዶ/ር አብይ ከኦሮሞ ውጭ ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ መስማት የሚፈልገውን ዲስኩር በተከሽነ አማርኛ እያንዶለዶሉ ለኦሮሞ ህዝብ ግን የሚፈልገው እንዲደረግለት የሚያስችሉ አሰራሮች እንዲዘረጉ እያደረጉ ነው። ለዚህ ደግሞ በርካታ ማስረጃዎች ማቅረብ ይቻላል። አንደኛ በሚንስትርነት፣ በምክትል ሚንስትርነትና በተለያዩ የፌዴራል መንግስት መስሪያ ቤቶች ደረጃ እንደ አዲስ እየተሾሙ ያሉት በብዛት የኦህዴድ ሰዎች ናቸው። እዚህ ላይ መታየት ያለበት እነዚህ የኦህዴድ ሰዎች በቁጥር መብዛታቸው ብቻ ሳይሆን የሚሾሙበት ቦታም የአገርን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎች ለመቆጠጠር ቁልፍና ወሳኝ ናቸው ተብለው የሚታመንባቸው እንደ ጠቅላይ አቃቤ ህግ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የገቢዎችና የመሳሰሉት ተቋማት መሆናቸው ጭምር ነው። የፀጥታ ተቋሙንም ቢሆን በነዚሁ የኦህዴድ ሰዎች ቁጥጥር ስር ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የሚያሳዩ ምልክቶች እየታዘብን ነው። ለምሳሌ የአየር ሃይል አዛዡና የሃገሪቱ የደህንነት ተቋም ሃላፊዎች የኦህዴድ ሰዎች ናቸው። የጦር ሃይሎች ጠቅላይ አዛዡ፣ መከላከያ ሚ/ሩና ም/ኤታማዦር ሹሙም የኦህዴድ ሰዎች ናቸው። እንዲያውም አሁን አሁንስ ከዋናው ኤታማዦር ሹም ይልቅ የኦህዴድ ሰው የሆኑት ምክትሉ ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።

በተጨማሪም አዲስ አበባን በቁጥጥር ስር ለማድረግ መታወቂያ በማደል፤ እንዲሁም መዋቅሩን ኦሮሟዊ ለማድረግ እንዲቻል የኦህዴድ ሰዎችን በመሰግሰግ እየተሴረ ያለው ሴራ ቀላል አይደለም። በአዲስ አበባ አዴፓ (ADP) ኮሚቴ የተሰጠው መግለጫ የሚያረጋግጠውም ይህንኑ ነው። የመታወቂያውን ጉዳይ በተመለከተማ ስራዋን ባግባቡ ለመወጣት በማሰብ ለሚድያ ተቋም መረጃ የሰጠች የመረጃና የወሳኝ ኩነቶች ሰራተኛ ከስራ እስከመታገድ ሁሉ ደርሳለች።  በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ላይ ያለውን ባለቤትነት ለማረጋገጥም ጊዜ እየጠበቁ እንደሆነ እነጃዋር ሳት ብሏቸው እያወጡ ካለው ምስጢር እየተረዳን መጥተናል።

ይህን ሴራ ለመሸፈን ደግሞ የእቅዱ አስፈፃሚ የሆኑት ዶ/ር አብይ በኢትዮጵያዊነት ስም የሚያደርጉትን ፍሬ የሌለው ስብከትና ትወና ቀጥለውበታል። በዚህ ረገድ የነዶ/ር አብይን ሰምና ወርቅ የሆነ የፖለቲካ ጨዋታ የተረዳው ርዕዮት የተባለ የፖለቲካ አቀንቃኝና ጋዜጠኛ የሚከተለውን መከራከሪያ አቅርቧል።

“[ባለፈው] ሰሞኑን በተለቀቀው Video ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስአበባን አስመልክቶ ከዚህ ቀደም ያራመዱት አቋም ከፓርቲያቸው የማይለይና አዲስአበባን ለአንድ ክልል ባለቤትነት አሳልፎ የሚሰጠውን ከፋፋይ ረቂቅ አዋጅ የሚደግፍ እንደነበር ተመልክተናል፡፡ …አሁን [ደግሞ]ኢትዮጵያንና ታላቅነቷን ባገኙት መድረክ ሁሉ መስበክ ጀምረዋል..”

 

በእርግጥ አሁን ላይ ከዶ/ር አብይ ይልቅ የኢትዮጵያን አንድነት ለማናጋት ቆርጦ የተነሳው እጅግ በጣም አስጊ ሆኖ ያለው በአቶ ለማ መገርሳ አጋፋሪነትና በጃዋር ስትራቴጅ አውጭነት የሚመራው ፅንፈኛ ሃይል ነው። ይህ ሃይል በአንድ በኩል አማራን አዳክሞ እና አግልሎ፤ በሌላ በኩል ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን ደልሎ ወይም አስፈራርቶ ከጎኑ እንዲሰለፉ በማድረግ የበላይነቱን ለመቆናጠጥ ሌት ተቀን እየሰራ ያለ ሃይል ነው። የአቶ ሽመልስ አብዲሳ የሰሞኑ ንግግርም ከዚሁ ፅንፈና ሃይል የሚቀዳ እሳቤ ነው።

ይህ ሁሉ ሲሆን የብአዴን (አዴፓ) ሰዎች ልክ እንደ ልሂቃኑ ሁሉ እየተሸወዱ ያሉት በእነ ዶ/ር አብይና አቶ ለማ በሚቀነቀነው ስብከት (ሰም) እንጅ እየተደረገ ባለው ድርጊት (ወርቅ) አይደለም። የሚያሳዝነው ደግሞ እነዚህ የአዴፓ ሰዎች ይህን በሴራ የተጠመጠመ ተግባር (ወርቅ) ቆፍሮ ለማግኘት እንኳን ብቃቱ ፍላጎቱም የሌላቸው መሆኑ ነው። የብቃት ነገር ሲነሳ አዴፓዎች በጣም ያሳዝኑኛል። ሌላው ይቅርና ተማርን የሚሉት እንኳ ሲማሩ በነበረበት ጊዜ ፈተና ለማለፍ ካጠኑትና ካነበቡት ውጭ ስትራቴጂክ የሆነ ሃሳብ ለማመንጨትና የክልሉን ብሎም የሃገሪቱን ህዝብ የተወሳሰቡ ችግሮች ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት አለ ለማለት ይከብዳል። ብቃት ያላቸውን የአማራ ምሁራንም ስልጣን ይጋፉናል ብለው ስለሚያስቡ አያስቀርቧቸውም። በዚህም ምክንያት ይመስላል ሙህራን አንድ መድረክ ላይ ምን እንርዳችሁ ብለው ሲጠይቁ የአዴፓ መሪዎች በበኩላቸው ድርጅቱ ውስጥ ገብታችሁ ትግሉን አጠናክሩት በማለት ፋንታ እዛው በያላችሁበት በየሙያችሁ ካገለገላችሁ በቂ ነው የሚል እንደምታ ያለው መልስ የሰጡት። ከዚህ አንፃር አሁን ባላንበት ከፍተኛ የውድድር ዘመን የአዴፓ ሰዎች እንዴት አድርገው የአማራን ህዝብ ጥቅም ሊያስጠብቁ እንደሚችሉ ፈጥሪ ነው የሚያቀው።

እነዚህ የአዴፓ ሰዎች የአማራ ሙህራንን በሰፊው በማሳተፍ ብቃታቸውን አሳድገውና ልቀው በመገኘት የአማራን ብሎም የኢትዮጵያን ህዝብ ችግር ለመፍታት ከመጣር ይልቅ የለውጥ “ሃይል በሚል” ባጋጣሚ በተገኘ ስም ተጀቡነው የኦህዴድ ሰዎች አጋፋሪ ሆነው ቀጥለዋል። ድሮም የብአዴን ሰዎች የህወሃት ሰዎች ቅጥ ሲያጡ ተው ብለው ወደ መስመር እንዲመለሱ ከማድረግ ይልቅ አጋፋሪዎች ነበሩ፤ ያሁኖቹ የአዴፓ ሰዎችም የተወረወርችላቸውን ፍርፋሪ ስልጣንና ጥቅም የሙጥኝ ብለው እግራቸውን ዘርግተው ተጎልተዋል። እየሆነ ያለው አዝማሚያ ያሳሰባቸው ሰዎች ሁኔታው እንዲስተካከል ጥያቄ ሲጠይቁ እንኳ እነ አቶ ገዱ የእኛ ትልቁ ጉዳይ ስልጣን አይደለም የሚል የፌዝ መልስ ሲሰጡ እየተደመጡ ነው። የሚገረመው ነገር ግን በህወሃት መራሹ ኢህአዴግ  ጊዜ የስልጣን ጥያቄ ከሚያነሱት ሰዎች ውስጥ ቁጥር አንድ የነበሩት እነ እነ አቶ ገዱ  የነበሩ መሆናቸው ነው። ምነው ታዲያ አሁን ትልቁ አጀንዳችን የስልጣን ጥያቄ አይደለም እያሉ ሰውን ለማሳመን ሲዳክሩ የሚሰሙት?

ዲያስፖራዎች፣ ተቃዋሚ ተብየ የፖለቲካ ስብስቦች፣ የሚዲያ ሰዎችና ሌሎችም በበኩላቸው መሰረታዊ የሆነ የአወቃቀር፣ የአደረጃጀት፣ የተቋማት፣ የአመራርና የአሰራር ለውጥ በሌለበት፤ እዚህም እዛም በሚደረጉ ለውጥ በሚመስሉ እርምጃዎች በመሸወድ ለውጡ እንዳይደናቀፍ በሚል አሁን በሃገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን ለማስተካከል የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ እምብዛም አይታዩም። ይህ መሆኑ ደግሞ የኦሮሞ ፅንፈኞች ያሻቸውን እንዲያደርጉ በር ከፍቶላቸዋል።

በአጠቃላይ ሲታይ እነ ዶ/ር አብይ በሰምና ወርቅ ፈሊጥ አይነት ፖለቲካ ጨዋታ የተዋጣላቸው ይመስላል። ሌት ተቀን የሚያቀነቅኑት ስብከት ሰሙ ኢትዮጵያዊነት ሲሆን ተጋባሮቻቸው (ወርቁ)  ደግሞ ኦሮሟዊ መሆኑን  የሚያሳዩ ምልክቶች በዝተዋል። ይህ አይነት ፖለቲካ ደግሞ የእርድና ፖለቲካ ከሞሆን አይዘልም። እኔ በተወለድኩበት አከባቢ አራዳ ሲባል ጭልፊት፣ አፈ ቂቤ፣ ጮሌ፣ አፈ ጮማ፣ ቂቤ ጠባሽ ወይም አማላይ ማለት ነው። በዚህ መንገድ የሚጠራ ሰው ብዙውን ጊዜ ከአፉ ክፉ አይወጣም። እንዲያውም ነብሴ፣ ሆዴ፣ እናቴ፣ ምን ልሁንልህ፣ ምን ይጠበስ፣ እኔ ልሙትልህ/አፈር ልሁንልህ፣ ካንተ በፊት እኔን ያድርገኝ ይልሃል። ይህ ማለት ደግሞ ሰም መሆኑ ነው።  የዚህ አይነት ሰው የተደበቀ አላማ ማለትም ወርቁ ግን ካንተ ላይ ሊያገኝ የሚፈልገውን የሚገባም ይሁን የማይገባ ጥቅም በተለሳለሰ መንገድ ማግኘት ነው።

የነዶ/ር አብይ በተለይ ደግሞ የአቶ ለማና የአጋሮቹ አላማም ይህ እንዳይሆን እጅግ በጣም ጥንቃቄና ብስለት በተሞላበት መንገድ መከታተል ይጠይቃል። ችግሮች በተከሰቱ ቁጥር ለህወሃት ካለ ጥላቻ ብቻ ተነስቶ ለውጡ እንዳይደናቀፍ በሚል ሰበብ አንገት ደፍቶ አፍ ሸብቦ አይቶ እንዳላዩ ማለፍ ትርፉ ተያይዞ ገደል መግባት እንጅ ሌላ ጥቅም አይኖረዉም። ይልቁንም እዚህም እዛም የሚታየው ልቅምቃሚ ለውጥ ሊጎለብት የሚችለው በጠንካራ መርህ ላይ የተመሰረተ ትግል ማድረግ ሲቻል ብቻ እንደሆነ ሁላችንም ልንገነዘብ ይገባል። በሌላ አነጋገር ከመሸ በኋላ ችግሩን ለመፍታት ባትሪ ፍለጋ ከመሯሯጥና ከመደናበር ይልቅ አሁኑኑ የሚታዩ ችግሮች እንዲፈቱ ያላሰለሰ ትግል በማድረግ ሁሉም ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእኩልነትና በሚዛናዊነት ያገባናል የሚሉበትና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲፈጠር፤ በአጠቃላይም የኢትዮጵያ አንድነት፣ሰላምና ዴሞክራሲያዊ እድገት እንዲጎለብት መስራት ይጠይቃል።

 

The post የኦህዴድ ሰዎች ፖለቲካዊ ሰምና ወርቅ   (ባዩህ ተስፋየ) appeared first on ሳተናው ዕለታዊ ዜናዎች:ጥናታዊ ጽሁፎችና ዝማኔዎች: መረጃ ማግኘት መብተዎ ነው!.


የኦህዴድ ሰዎች ፖለቲካዊ ሰምና ወርቅ   (ባዩህ ተስፋየ)