ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር የመጀመሪያ የሆነ በሞት የሚያስቀጣ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ አስተዳደር የመጀመሪያ የሆነ በሞት የሚያስቀጣ ድንጋጌን የያዘ ረቂቅ አዋጅ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን ይሁንታ አግኝቶ ሐሙስ መስከረም 29 ቀን 2012 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ለምክርቤቱ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ እንደሚያስረዳው በሰዎች የመነገድ፣ በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገርና በሕገወጥ መንገድ ለሥራ ሥምሪት ወደ ውጭ አገር መላክ ወንጀሎች የሰዎችን አካል፣ ሕይወትና ደኅንነት ለአደጋ የሚያጋልጡ ወንጀሎች በመሆናቸውና እነዚህን ወንጀሎች መከላከል አስፈላጊ መሆኑ እንዲሁም በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ቁጥር 909/2007 ግልጽነት የጎደለው፣ ከሌሎች ሕጎች ጋር የማይጣጣምና ለችግሩ በቂ ምላሽ የማይሰጥ ሆኖ በመገኘቱ በአዲስና በተሟላ የሕግ ማዕቀፍ መተካት አስፈላጊ መሆኑ ታውቋል፡፡
በረቂቁ ድንጋጌ መሠረት ብዝበዛ ማለት “ሌላውን ሰው ከፈቃዱ ውጭ ወይም ሙሉ ፈቃዱን መስጠት የማይችል ወይም ፈቃዱን መስጠት በማይችልበት ሁኔታ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አካሉን፣ ሥነ ልቦናውን ወይም ኢኮኖሚውን በመቆጣጠር ለራስ መጠቀም ወይም ሌላ ሰው እንዲጠቀም ማድረግ ሲሆን፣ በተለይም በወሲብና ወሲብ ነክ ተግባር ማሰማራት ወይም መፈጸም እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
ማንኛውም ሰው፣ በሰው የመነገድ ወንጀልን የፈጸመ እንደሆነ ከ5-10 ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ10 ሺሕ ብር እስከ 50 ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚቀጣና ድርጊቱ የተፈጸመው በሕፃናት ወይም በአካል ጉዳተኞች ላይ ከሆነ፣ እንዲሁም በመንግሥት ሠራተኛ ከሆነ ቅጣቱ ከ10 እስከ 18 ዓመት የሚደርስ ፅኑ እስራትና ከ30 ሺሕ እስከ አንድ መቶ ሺሕ ብር በሚደርስ መቀጮ እንደሚሆን ረቂቁ ይገልጻል፡፡
ወንጀሉ በተጎጂው ላይ ሞትን አስከትሎ ከሆነ ቅጣቱ ከ20 ዓመት እስከ ዕድሜ ልክ ፅኑ እስራት ወይም በሞትና ከመቶ እስከ ሦስት መቶ ሺሕ ብር እንደሚያስቀጣ በረቂቁ ተደንግጓል፡፡ እነዚህን ወንጀሎች መከላከልና መቆጣጠርን ዓላማው ያደረገ ብሔራዊ አስተባባሪ ምክር ቤት እንደሚቋቋምና ተጠሪነቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚሆን በረቂቁ ተመልክቷል፡፡ ፓርላማው ረቂቅ አዋጁ ላይ ውይይት ካደረገ በኋላ ለሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል፡፡
ረቂቁ በዚሁ መልኩ የሚፀድቅ ከሆነ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዓብይ አህመድ የሥልጣን ዘመን የመጀመሪያ የሚሆን፣ እንዲሁም ለመጀመሪያዋ የአገሪቱ ሴት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለፊርማ የሚቀርብ የሞት ቅጣትን የያዘ አዋጅ ይሆናል፡፡


ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር የመጀመሪያ የሆነ በሞት የሚያስቀጣ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ ፡፡