“ስርየት አልባ ወንጀል!” – ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ

Satenaw: Ethiopian News & Breaking News: Your right to know!

ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ
የኢኮኖሚክስ መምህርና ጸሓፊ
(ሸክም የበዛበት ትውልድ፡ 2009 እና
የምሥራቃዊት ኮከብ፡ 2010 መጻሕፍት አዘጋጅ)

በማንኛውም ዓይነት የሕብረተሰብ መስተጋብር ውስጥ ወንጀል የነበረ፣ ያለና የሚኖር ተርዕዮ ነው፡፡ የወንጀሉ ዓይነት፣ መጠን፣ ስፋት፣ አድማስ፣ ተጽዕኖና ህልውና ከፈጻሚውና ከተፈጸመበት አካል አንጻር የተለያየ ኾኖ ወንጀል በግለሰብ/ቦች፣ በቡድን/ኖች እንዲሁም በተቋማት ሊፈጸም ይችላል፡፡

ወንጀል – ምንጊዜም ተቀጥላዎች – ከባድ፣ መካከለኛና ቀላል አልያም የታሰበበትና ያልታሰበበት፤ በማወቅና ባለማወቅ፤ በውዴታና በግዴታ ቢፈጸምም ወንጀል – ወንጀል ነው፡፡ ወንጀል በህሊና፣ በህግና በታሪክ ያስጠይቃል፡፡

ይህ ከላይ የተጠቀሰ ገለጻ ማንም በቀላሉ የሚረዳውና የሚያውቀው ዕውነት (Truth) እና እውነታ (Reality) ቢኾንም በአንድ መንፈሳዊ ቦታ ከሚኖሩ ስለሀገራችንም ኾነ ዓለማችን መሠረታዊ ዕውቀት ካላቸው አባት ጋር በአጋጣሚ ስንወያይ፡-

አባት፡ “ልጄ – የሀገራችንን ነባራዊ ኹኔታ እንዴት ታየዋለህ?” አሉኝ፡፡

እኔ፡ “የሀገራችን የሥልጣን ፖለቲካ በዚሁ ከቀጠለ አኳኩሉና እቃቃ ጨዋታ በUNESCO ይመዝገብልን እንደሚያስብል ስናስብ – ‘ህጻንነት’ ለማኗኗር ትኑር! አልን አባቴ” – አልኩኝ – የማውራት ፍላጎት እንደሌለኝ በሚያሳብቅ ቅላጼ – እሳቸው ከልብ ሳቁ – ገረመኝ፡፡ በአድናቆት ተመለከትኳቸው፡፡ ደግመው ደጋግመው “ወይ – ጉድ – ወይ – ጉድ” እያሉ ከቆዩ በኃላ “ልጄ – ስርየት አልባ ወንጀል ታውቃለህ?” አሉኝ፡፡

እኔ፡ “አላውቅም!”

አባት፡ “ሁለት አይነት ወንጀሎች ስርየት አልባ ናቸው፡፡”

እኔ፡ “ምንና ምን?”

አባት፡ “በፍቅርና በሀገራዊ ትውልድ/ዶች ላይ የሚሰሩ ወንጀሎች”

እኔ፡ “እንዴት?”

አባት፡ “በፍቅር የሚሰራ ወንጀል – በፈጣሪ ስም የሚሰራ ወንጀል ማለት ነው፡፡”

እኔ፡ “ማለት?”

አባት፡ “ይኸውልህ አንድ ወንድ – አንዲት ሴትን የዕውነት ሳያፈቅር አፈቅርሻለው ይላታል፡፡ እሷም አምናው፣ ተቀብላው – ማድረግ ያለባትን ኹሉ ታደርጋለች፡፡ በጊዜ ሂደት ያ ወንድ ይዋሻታል፣ ይደብቃታል፣ ያስመስላል፣ ከሌላ ሴት ጋር ይገናኛል፣ ይባስ ብሎ እሷን አለም እንዳልገባት ፋራ ቆጥሮ የዋህነቷን እንደጅልነት፤ ግልጽነቷን እንደስንፍና፤ መስዋዕትነቷን እንደፋራነት በማየት ከዕለታት በአንድ ቀን ‘በማፍቀሬ እርግጠኛ አይደለሁም’ አላት፡፡”

እኔ፡ “እንዴ አባቴ ይሄማ የምናውቀው፣ የለመድነው፣ አዲስ ያልኾነና በአንጻሩ ፋሽን የኾነ የሰው ጸባይ አይደል?”

አባት፡ “ይኾናል – ልጄ!”

እኔ፡ “ታድያ አባቴ ይህን እንዴት እንደወንጀል ቆጠሩት – ያውም እንደስርየት አልባ?”

አባት፡ “ልጄ ያች ልጅ ምን ሊሰማት እንደሚችል አስበሃል?”

እኔ፡ “መከዳት”

አባት፡ “በቃ?

እኔ፡ “ሌላ ምን ሊኖር ይችላል?”

አባት፡ “ብዙ ነገር!”

እኔ፡ “ምን?”

አባት፡ “ልጄ ያች ሴት ያን ሰው አምናዋለች፣ አውቃዋለች፣ ብዙ ነገር አድርጋለታለች፡፡ ስለኾነም ልክ ስትከዳ – በዛ ሰው ላይ ብቻ ሳይኾን በፍቅሯ ላይ ያላት እምነቷ፣ እውቀቷ፣ ተስፋዋ፣ ስሜቷ፣ ድርጊቷና ትዝታዋ በሙሉ ይጠፋል፡፡”

እኔ፡ “እ – እ – እ”

አባት፡ “ልጄ ሰውን መክዳት ቀላል ነው፡፡ ሰውን ማታለል ቀላል ነው፡፡ ሰውን መለወጥ እጅግ ቀላል ነው፡፡ በአንጻሩ ግን ከመከዳት፣ ከመታለል፣ ከመለወጥ በኃላ ወደ ቀደመ ማንነት ለመመለስ ከባድ ነው፡፡ ከባድም ወንጀል ነው፡፡ ሰዎች እንደቀላል ያዩታል ነገር ግን ስርየት አልባ ወንጀል ነው፡፡ ፈጣሪ ፍቅር ነው፡፡ በፍቅር ስም የሚሰራ ወንጀል ስርየት አልባ ወንጀል ነው፡፡”

እኔ፡ “መልካም! ሁለተኛውስ?”

አባት፡ “ሁለተኛው በትውልድና ትውልዶች ላይ የሚፈጸም ወንጀል ነው፡፡”

እኔ፡ “እሱስ እንደምን ያለ ነው?”

አባት፡ “ይህ በዓይነቱ ለየት ያለ በአብዛኛው በፖለቲካ አካባቢ የሚፈጸም ወንጀል ነው፡፡”

እኔ፡ “እንዴት?”

አባት፡ “ድርጊቱ በማወቅም ይኹን ባለማወቅ፤ በንቃትም ኾነ ያለ ንቃት፤ በፍቃደኝነትም ይኹን በግዴታ የሚፈጸም ትውልድንና ሀገርን የሚጎዳ ተግባር ለአብነት፡- የሀገር ሉዓላዊነት፣ የሀገር ሀብት፣ ድንበር፣ በሀገር ምስጢር ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን የሚይዝ ነው፡፡”

እኔ፡ “ይህማ እንደጸጉራችን ብዛት ብዙ አይደለምን?”

አባት፡ “ልጄ ይመስለናል እንጂ እንዲህ አይነት ነገሮች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ለአብነት፡- ሀገራዊ ውሎችና ስምምነቶችን የሚመስሉ ናቸው፡፡ የውጫሌ ውል ሀገርን ኹለንተናዊ ዋጋ እንዳስከፈለው አይነት ያሉ ውሎች ማለት ናቸው፡፡”

እኔ፡ “የታሪክ?”

አባቴ፡ “የታሪክ ብቻ ሳይኾን ተሻጋሪ ናቸው፡፡”

እኔ፡ “ማለት?”

አባት፡ “ከዛ በኃላ የተከሰቱ ነባራዊ ኹለንተናዊ ኹኔታዎቻችንን ካስተዋልክ በቀጥታም ይኹን በተዘዋዋሪ የዛ መዘዝ እጅግ የበዛ ነው፡፡ ተጽዕኖውም እጅግ የበዛ ኾኖ ታገኘዋለህ፡፡ የዓድዋ ጦርነት ከዚ ውል ይወለዳል፡፡ ድሉ ከዚህ ጦርነት ይወለዳል፡፡ ከድሉ በኃላ የተቀየሩ የሀገራችንም ኾኑ የአለማችን ኹነቶች ከዛ በኃላ ይወለዳሉ፡፡ የመዋለዱ ብዜት እንኳንስ ትላንት ዛሬ ላይ እንኳ ላለችው ኢትዮጵያና ከባቢዋ የሚታይ ነው፡፡”

እኔ፡ “እጅግ በጣም!”

አባት፡ “አየህ ልጄ የ21ኛው ክፍለ ዘመን የውጫሌ ውል ስላለመዋዋላችን አልያም ልንዋዋል እንዳልኾነ ምን ማረጋገጫ አለ?”

እኔ፡ “ምንም!”

አባት፡ “ትውልድን ብቻ ሳይኾን የትውልድ ትውልድ ላይ አሉታዊ ማቋረጫ የሌለው ተጽዕኖን የሚያሳርፍ ወንጀል ስርየት አልባ ወንጀል ይባላል፡፡ ያለህበት ብቻ ሳይኾን የሚመጣው ትውልድ ይጠይቅሃል፡፡ የሚመጣው ብቻ ሳይኾን ከዛ በኃላ የሚመጡ ትውልዶች ኹሉ ይጠይቁሃል፡፡”

እኔ፡ “እውነት ብለዋል!”

አባት፡ “ስርየት አልባ ወንጀሎች በህሊና፣ በስሜት፣ በህግ፣ በታሪክ፣ በትውልድ ብቻ ሳይኾን ከሞት በኃላም ቢኾን በፈጣሪ ዘንድ የሚያስጠይቁ ናቸው፡፡ ሲፈጸሙ ቀላል ይመስላሉ – ተጽዕኗቸው ግን እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፡፡”

እኔ፡ “በጣም!”

አባት፡ “ልጄ ከስርየት አልባ ወንጀሎች ራስህን ጠብቅ!”

እኔ፡ “እሺ”

አባት፡ “ስርየት አልባ ወንጀል ምድራዊ ብቻ ሳይኾን ሰማያዊ ቅጣት ያስከትላል፡፡ የወንጀሉ አካል መኾን መዥገርነት አለፍ ሲልም ትውልዳዊ መዥገር መኾን ነው፡፡”

እኔ፡ “ከባድ ነው፡፡”

አባት፡ “ልጄ ስናወራው የከበደን ሲሰራብን እንዴት ይቻላል? ብሎ ማሰብ ብልህነት ነው፡፡”

እኔ፡ “አባቴ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡ እጅግ በጣም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡”

አባት፡ “ፈጣሪ ካንተ ጋር ይኹን!”

እኔ፡ “አሜን!” ብዮ ተለየኋቸው፡፡ ምንም እንኳ ርዕሰ ጉዳዩ ከባድ ቢኾን እጅግ በቀላሉ ጥበብ በተሞላበት ገለጻ መገለጹ ለብዙዎቻችን አስተማሪ ይኾናል በሚል አቀረብኩት፡፡

  ሀገራችን ፍጹም ከወንጀል ነጻ ልትኾን ባትችልም ቢያንስ የወንጀሎቹ ዓይነት፣ መጠንና አድማስ የከፋው እና ስርየት አልባው እንዳይኾን ምን እያደረግን ይኾን? ከወንጀሎች ኹሉ የከፋው ትውልዶችን ዋጋ የሚያስከፍል – ከትውልድ ወደ ትውልድ ማለቂያ በሌለው ሰንሰለት ውስጥ የሚከት – ወንጀል እንዳይፈጸም እያስተዋልን ይኾን? በምን? እንዴት? መቼ? በማን? ሀገር ከስርየት አልባ ወንጀል ትጸዳ ዘንድ ሀገራውያን እንቅልፍ ሊያጡ የሚገባ መኾኑን ማን ይስታል? ፈጣሪ ሀገራችን ነጻ ፍቃድን የኹሉ ነገር ማዕከል ወደ ሚያደርግ የዕሳቤ ሂደት ትገባ ዘንድ ይርዳን!

ቸር እንሰንብት!

The post “ስርየት አልባ ወንጀል!” – ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ appeared first on ሳተናው ዕለታዊ ዜናዎች:ጥናታዊ ጽሁፎችና ዝማኔዎች: መረጃ ማግኘት መብተዎ ነው!.


“ስርየት አልባ ወንጀል!” – ፀጋዝአብ ለምለም ተስፋይ