የምዕራብ ኦሮሚያ ቴሌኮም አገልግሎት መከፈት እና የኮቪድ 19 ስጋት::

አባይ ሚዲያ መጋቢት 22፤2012

በምዕራብ ኦሮሚያ ተቋርጦ የነበረው የቴሌኮም አገልግሎት እንዲከፈት ተወሰነ  የኦሮሚያ ክልል መንግሥት በምዕራብ ኦሮሚያ ተቋርጦ የነበረው የቴሌኮም አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ እንዲከፈት መወሰኑን አስታወቀ።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ሽመልስ አብዲሳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ባለፉት ቀናቶች በምዕራብ ኦሮሚያ በአራቱ የወለጋ ዞኖች በተለይም በቄለም ወለጋ፣ ምእራብ እና ምስራቅ ወለጋ እንዲሁም ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ባደረጉት ጉብኝት አካባቢዎቹ ወደ ሰላም እና መረጋጋት መመለሳቸውን ገልጸው ተቋርጦ የነበረው የሞባይል ኢንተርኔት እና የሰልክ አገልግሎት ከዛሬ ጀምሮ እንዲከፍት መወሰኑንም ጠቁመዋል።

ከኮቪድ 19 ስርጭት ጋር በተያያዘ በኦሮሚያ ክልል የቴሌኮም አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢው ስለ ወረርሽኙ መረጃ ያገኙ ዘንድ የቴሌኮም አገልግሎቶች ክፍት እንዲሆኑ በርካቶች ሲጠይቁ እንደነበረ ይታወሳል።

በተያያዘ ዜና አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ የአውቶብስ መናሀሪያዎች በመዘጋታቸው በርካታ ተጓዦች እንግልት እየደረሰብን ነው ብለዋል በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡

በመሆኑም ድንገት በሚባል ሁኔታ የኦሮሚያና የአማራ ክልላዊ መንግስታት የሰዎችን ከቦታ ቦታ እንቅስቃሴ ለመግታት በማሰብ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ እንቅስቀሴዎችን በአስቸኳይ ገድበዋል።

በተለይም አዲስ አበባ በሚገኙት የላምበረት ፣አውቶቡስ ተራ፣ አስኮ እና ሌሎች መነሀሪያዎች ሙሉ በሙሉ የተዘጉ ሲሆን የመናሀሪያዎቹ በርም በፌደራል ፖሊስ እየተጠበቀ ይገኛል፡፡

በሩ ላይ በአዲስ አበባ የቀን ስር ሲሰሩ የነበሩ በስራው መቀዝቀዝ ምክንያት ወደ ቤተሰቦቻቸው መሄድ የሚፈልጉ፣ ከዩንቨርሲቲዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለህክምና መጥተው ወደ ቤታቸው መመለስ የፈለጉ ሰዎች በትራንስፖርት እጥረት ተቸግረው እየተንገላቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

መንገደኞቹ መንግስት የወሰደው እርምጃ ዱብ እዳ እንደሆነባቸው እና ክልሎች የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ እንቅስቀሴዎች ላይ ገደብ ከመጣላቸው አስቀድሞ በጥቂቱ 3 የእፎይታ ቀናቶች ሊሰጡን በተገባ ነበር ያሉ ሲሆን ያ ካልሆነ ግን ቢያንስ ጊዜያዊ ማቆያ ሊዘጋጅልን ይገባ ነበር በማል ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡

ይህ ሁሉ በሌለበት ሁኔታ እገዳው እስኪነሳ ቀርቶ አንድ ቀን እንኳን ሊያሳድር የሚችል ገንዘብ እጃቸው ላይ እንደሌለ ነው እንግልት ደረሰብን የሚሉት ተጓዦች የሚናገሩት፡፡


የምዕራብ ኦሮሚያ ቴሌኮም አገልግሎት መከፈት እና የኮቪድ 19 ስጋት::