የታለቁ ህዳሴ ግድብ የእንቦጭ አረም ስጋት፡፡

አባይ ሚዲያ ግንቦት 15፤2012

ጣና የዓለም የብዝሃ ህይወት ሀብት ሆኖ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስ እና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በ 2007 ዓ.ም የተመዘገበ ቢሆንም፤ በመጤው የእንቦጭ አረም እየተጠቃ በመምጣቱ የአካባቢውን ነዋሪዎችና የቱሪዝም ባለሙያዎችን ስጋት ላይ ከጣለ ሰንብቷል፡፡

የውሃ ስነ ምህዳር ተመራማሪውና በአሁኑ ወቅት የጣና ሐይቅና ሌሎች ውኃማ አካላት ጥበቃና ልማት ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አያሌው ወንዴ እንቦጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በሃይቁ ላይ መኖሩ የተረጋገጠው ነሀሴ ወር 2003 ዓ.ም መሆኑን እና መስከረም 2004 ዓ.ም የውኃ ስነ ምህዳር ተመራማሪዎች የእንቦጭ አረም መከሰቱን ለክልሉ መንግስት ማስታወቃቸውን ተናረዋል፡፡

በዓለም ላይ የጣና እንቦጭን ያህል በአጭር ጊዜ፣ ሰፊ ቦታን የሸፈነ አረም በዓለም ላይ የለም ያሉት ተመራማሪና ሃላፊው በግብጽ እና በሱዳን የተከሠተው የሀይቁን መሀል የሚጐዳ አልነበረም ብለዋል የጣናው እንቦጭ ግን የአካባቢውን ብዝሀ ህይወት ሙሉ በሙሉ አውድሞ የውሀውን ህልውና ሁሉ የሚያጠፋና ጣናን የብስ (ደረቅ መሬት)የማድረግ ጉልበት እንዳለው ዶክተር አያሌው ይገልጻሉ፡፡

በጣና ሃይቅ ላይ የተንሰራፋውን እምቦጭ ለማጥፋት ከፍተኛ ስራ እየሰሩ የሚገኙት አርሶ አደሮች መሆናቸው የሚገለጽ ቢሆንም አረሙን ለማጥፋት ገንዘብ ስለሚከፈላቸው አረሙን ቶሎ ማጠናቀቅና አለማጠናቀቅ ከገንዘቡ ጋር ይያያዛል የሚሉ አስተያየቶች እንደሚሰሙና አሁን ላይ አረሙን ለማጥፋት ለአርሶ አደሮች ተለክቶ እንደሚሰጥ  ዋና ስራ አስኪያጁ አረጋግጠዋል፡፡

ዶ/ር አያሌው ወንዴ የእምቦጭ አረም የጣና ሃይቅን ወደ 4ሺ ሄክታር ይዞታ ሸፍኖት የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ግን 1 ሺ ሄክታር የውኃ ክፍልን መሸፈኑን አስታውቀው አረሙን ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት ታስቦ እንደነበርና አሁን ላይ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እንዳስተጓጎለው ተናግረዋል፡፡

አርሶ አደሮች አረሙን ለማጥፋት እየሰሩ ያለው ስራ ከሁሉም በላይ ውጤታማ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር አያሌው ከህዳር ጀምሮ በ7 ወረዳዎች ላይ ከፍተኛ ስራ ለመስራ ታስቦ በአምስቱ ላይ ሲሳካ በሁለቱ አልተሳካም ብለዋል ከዚህ ቀደም ሀይቁን ለመታደግ የተገዙና በዩኒቨርሲቲዎች የተዘጋጁ ማሽኖች ካለው ችግር ጋር የመገናኘት ጉድለት እንዳለባቸው ያነሱት ሃላፊው ማሽን ሲመጣ ከሀይቁ ባህሪ ጋር መዛመድ አለበት ብለዋል፡፡

ሃይቁ የህዳሴው ግድብ  መሰረት መሆኑን የሚያነሱት ዶ/ር አያሌው ይህ አረም ቶሎ የማይጠፋ ከሆነ ወደ ህዳሴው ግድብ ሊጓጓዝ እንደሚችል ጠቁመው ፣ይህ አረም ወደ ግድቡ የግንባታ ሥፍራ ሳይደርስ እንደማይቀርም ግምታቸውን ተናግረዋል፡፡ እናም ዜጎች ስለግድቡ ያላቸው ብሔራዊ ስሜት ከውሃው መነሻ ጣና ሊጀምር ይገባል ሲሉ ሃሳባቸውን ገልጸዋል፡፡


የታለቁ ህዳሴ ግድብ የእንቦጭ አረም ስጋት፡፡