የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ “ስቴም-ፓወር” ከተባለ ተቋም ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ /ኢመደኤ/ “ስቴም-ፓወር” ከተሰኘ በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ እና በሒሳብ ዘርፎች ዙሪያ ከሚሰራ ተቋም ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ።

የመግባቢያ ሰነዱ ስቴም-ፓወር ከሚሰራባቸው ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና በሒሳብ ዘርፎች ዙሪያ  ታዳጊዎችን የማብቃት ሥራዎች ላይ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው ነው ተብሏል።

በኢመደኤ በኩል በስምምነት ሰነዱ ላይ ፊርማቸውን ያኖሩት የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው÷ ስምምነቱ ኤጀንሲው ከፍተኛ የፈጠራ አቅም ያላቸውን ታዳጊዎችን በመደገፍ በሳይበር እና የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ ለሚሠራው ሥራ ጉልህ አስተዋፅዎ የሚያበረክት ኃይል ለመፍጠር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሳይበር ደህንነትን ለማረጋገጥ ኤጀንሲው በራሱ ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ በርካታ ተዋኒያን በዘርፉ እንዲሳተፉ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው÷በተለይም የሥራ ዕድልን እንዲፈጥር፣ ዘርፉ በራሱ ምርት እንዲሆን፣ አገልግሎት እንዲሰጥ እንዲሁም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ተፅዕኖው የጎላ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ ስምምነቱ እገዛ እንደሚኖረውም ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡

በስምምነቱ ወቅት “የስቴም-ፓወር” ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ ቅድስት ገብረአምላክ÷ ድርጅታቸው በሳይንስ፣ በቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ እና በሒሳብ ሥራ የፈጠራ አቅም ያላቸው ህጻናትንና ወጣቶች የተግባር ተኮር እገዛ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።

ከኢመደኤ ጋር የተደረገው ስምምነትም በድርጅታቸው በፈጠራ ሥራ ድጋፍ እየተደረገላቸው ከሚገኙ ታዳጊዎች መካከል በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ከፍተኛ አቅም ያላቸውን ወጣቶች ለኤጀንሲው እሴት እንዲሆኑ ዕድል የሚፈጥር ነው ሲሉ ስራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል።

በሁለቱ ተቋማት በኩል የተደረገው ስምምነት ከ3 እስከ 5 ዓመት እንደሚቆይም ነው የተነገረው።

በቅርቡ በዶክተር ሹመቴ ይፋ የሆነው አዲስ ቴክኖሎጂ ዴቨሎፕመንት እና ፕሮዳክት ኮሜርሻይሌዜሽን ሮድ ማፕ ተቋሙ በሳይበር ደህንነት ዘርፍ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን ታዳጊዎችን እና ወጣቶቸን ማብቃት ስራ አንደሚሰራ ይፋ መሆኑ ይታወሳል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በተቋሙ በቅርቡ የሳይበር ተሰጥኦ ውድድር እንደሚዘጋጅ እና የፈጠራ አቅም ያላቸው ወጣቶች እንዲሣተፉ  ይደረጋልም ነው የተባለው።

“ስቴም-ፓወር” ከፍተኛ የፈጠራ ሥራ አቅም ላላቸው ተዳጊ ወጣቶች ተግባራዊ ሥራ መስራት የሚያስችላቸውን የማሽነሪ አቅርቦት የማመቻቸት፣ ግብዓት የማቅረብ፣ ሙያዊ አማካሪዎችን የመመደብ እና ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር የማገናኘት ሥራዎች በዋናነት እንደሚሰራከኢመደኤ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

#FBC

የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።


የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ “ስቴም-ፓወር” ከተባለ ተቋም ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረመ