ዝማሬና ውዳሴ የሚገባቸው ጀግኖች

 

lelisa and Ejiguሥጋት የሌለበት ሕይወት መኖር የሰው ልጅ የምንጊዜም ፍላጎት ነው:: ሥጋት ካለ የውስጥም ሆነ የውጭ ሠላም የለም:: ለጀግናው አትሌት  ለፈይሳ ሌሊሳ የመኖር ሥጋት  የሚመነጨው ከሚያየውና እና ከሚሰማው አስቀያሚ  ድርጊቶች ነው:: እስር: እንግልት: ሥቃይ: ወከባ:  ድብደባ: ቶርች  እና ግድያ  የተንሰራፋባት ኢትዮጵያ  የመኖር ህልውናን ሥጋት ውስጥ የሚጥሉ ናቸው::  ሰብዓዊ ስሜት ላለው ሰው ይህን ሁሉ ግፍ እና መከራ እየተመለከቱ ሠላማዊ ኑሮ አለኝ ማለት የጤና አይሆንም::

ፈይሳ ሌሊሳ ይህንን ነው ዓለመ- አደባባይ ላይ ያወጀው:: ፈይሳ በራሱ በግሉ ሕይወት የጎደለበት ሰው አይደለም:: ምርጥ መኪና: ምርጥ ቤት: ሙሉ ቤተሰብ  አለው:: በኢትዮጵያ የኮከብ አትሌቶች የኑሮ ሁኔታን  ማየቱ በቂ ነው::  ችግርተኛ: ስፖርተኛ: በሩዋጮች ዘንድ የለም:: ይታወቃል:: ኑሮውን ለመለወጥ እራሱን ለማሻሻል ሲል ጥገኝነት ፈለገ የማያስብለው ነው :: ዓለምን ያካለለ ለጋ ወጣት ነው:: ወዴትም መሄድ የሚችል ነው:: ለእርሱ ዜግነት አበርክቶ ለራሳቸው አገር እንዲሮጥና የራሳቸውን ሰንደቅ ዓላማ እንዲያለበልብላቸው የማይመኙ ሀብታም አገሮች የሉም::

የፈይሳ ሌሊሳ ችግር የወገኖቹ ችግር ነው:: የዜጎቹ ችግር ነው::  የሚሞቱት አማራ  ኢትዮጵያዊያን: የሚጨፈጨፉት ኦሮሞ ኢትዮጵያዊያን:  የሚረግፉት ጋምቤላዊያን  ወገኖቹ የውስጥ ሠላም አሳጥተውታል:: ይህን የህዝብ መከራና ሥቃይ እያየ አደገ:: እስከመቼ የሚል ጥያቄ እውስጡ ተጸነሰ:: ማብቂያ የት ይሆን ብሎ አሰበ::  ተጨነቀ:: ተጠበበ:: አረረ:: ከሰለ :: በገነ::  ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን በችግር ሲሰቃዩና እርሱ በሚሰቃዩ ወገኖቹ ላይ ውድ መኪና ማሽከርከር ደስታን አልፈጥርለት አለው:: የእርሱ እና የቤተሰቡ የተመቻቸ ኑሮ ብቻውን ትርጉም አሳጣው:: ብቻውን ጣዕም የለሽ ሆነበት:: የእውነተኛ ሰው  ሰብዓዊ ስሜት  ሰረጸበት::

ፈይሳ ይህንን ጭንቀቱን እንዴት ማቃለል እንደሚቻል አጠነጠነ::  አወጣ:: አወረደ::  ወያኔን በምን መልኩ ማጥቃት እንደሚቻል አሰላሰለ::  ለኢትዮጵያ ሕዝብ እውነት ስለማይነገረው  በሐሰት ወሬ ነጋ ጠባ  ሲጨቀጨቅ ሕዝብ አያውቅም ተብሎ ሀቅን መደበቅ ወይም ሕዝብ እውነትን እንዳያገኝ እንዳይፈልግ  አድርጎ በማፈን በአምባገነን አገዛዝ ሥር እንዲረገጥ ሲደረግ ፈይሳን አሳመመው:: እንቅልፍ ነሳው::  ስለዚህ ጀግና መቼ እንዴት እና በምን ዓይነት ታክቲክ ጠላቱን እንደሚያጠቃ ያውቃል::

ፈይሳም ይህንኑ አንድ ጀግና ምን ማድረግ እንዳለበትና ሃላፊነቱን መወጣት እንደሚችል ለማረጋገጥ  የደቡብ አሜሪካ ታላቅዋን የፔሌን አገር ብራዚልን መረጠ::

በሪዮ ዲዣኔሮ በኦሎምፒክ አደባባይ  የዓለም ዓይን ሁሉ የሚያርፍበት ቅጽበት ለማግኘት ተግቶ ሠራ::  መመዘኛውንም አልፎ ብራዚል ገባ::

የልቡን በልቡ ይዞ ማራቶን ሩጫውን ጀመረ::  ፈይሳ በዓይነ ህሊናው  የሚሞተውን: የሚደበደበውን: የሚታፈሰውን: የሚታሰረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ እያየ  ይሕ ሕዝብ ሠላም ነው ብሎ እራሱን ዋሽቶ  እና እራሱን አሞኝቶ የኦሊምፒክን ዓላማ ማሳካት አልፈለገም:: ጥሬ እውነትን ለኦሎምፒክ አባላትና ታዳሚ ሁሉ መንገር እንደሚሻል አስቀድሞ ስላሰበ እርሱ የሚሮጥለት ሕዝብ እያለቀ መሆኑን  ማሳወቅ ነው::  ፈይሳ ይህንን አደረገ::  እኔ ስሙን በክብር ለማስጠራት የምሮጥለት ሕዝብ እየሞተ ነው አለ::    በኦሮሚያ ሕዝብ የተቃውሞ ምልክት ተደርጎ የተወሰደውን የተጣመረ የእጅ ምልክት  ደጋግሞ  አሳየ:: የኢትዮጵያ ሕዝብ ገዳይ የሆነው ዓርማ ያለበት ባንዲራን ማውለብለብ ነፍሰ ገዳይን  ማበረታታት ስለሆነ እምቢ አለ::

የዓለም ሕዝብ ግራ ተጋባ::  እንደ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ መረጃ ከሆነ በ32 ሴክንድ ብቻ ከአስር ሚሊዮን በላይ የዓለም ሕዝብ ፈይሳን ተመለከተ:: የሚያሳየውን የተቃውሞ ምልክት ተመለከተ እና ዓለም ምንድን ነው  ብሎ ጠየቀ::  ወዲያው የዓለም ጋዜጠኞች ለፈይሳ ጥያቄ አቅርበውለት ምስጢሩን ገለጡት:: የዓለም ሕዝብ ቆይ እስቲ ብሎ  ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ፊቱን አዙሮ ለማየት ሞከረ:: እናም በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን  ይደረጋል ብሎ የማያስበውን ጉድ አየ:: ይህን የሚያደረግ ደግሞ መንግስት ነኝ ባዩ ሆኖ ሲገኝ የዓለም መንግስታት ሁሉ  ስለኢትዮጵያ መንግስት አንገታቸውን ደፉ::  ኢትዮጵያ  በኦሊምፒክ አደባባይ እንዳልተደነቀች: እንዳልተከበረች ሁሉ ውርደትም ተከናነበች::  ዕድሜ ለወያኔ የኢትዮጵያ ታሪክ ጥላሸት ተቀባ:: ዕድሜ ለፈይሳ ሌሊሳ ግፈኛው ሥርዓት  ተጋለጠ::

ወኔ ካለ: ልብ ካለ:  ወገናዊ ስሜት ካለ በኦሊምፒክ አደባባይም  ታሪክ መስራት እንደሚቻል የጀልዱ ልጅ ፈይሳ አሳየ:: መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የታመቀ ብሶቱን በፈይሳ በኩል ለዓለም ተነፈሰ::   የወያኔ ሥርዓትም በኦሊምፒክ አደባባይ መብረቅ ወረደበት::

እንግዲህ እኛ የእትዮጵያ ሕዝብ ሚሊዮኖች ሆነን ያቃተንን ነገር አንድ ሰው ፈጸመው ማለት ስለማይበቃ ትንግርት ሠርቶ አሳየ:: ሰው ማለት ሰው ሆኖ  መገኘትሰው የጠፋ ዕለት ማለት እንዲህ ነው ::

 

የፈይሳ እናት ውለጅ መንታ መንታ:

በግራው ሜዳሊያ በቀኙ ጠላት የሚመታ:

 እነ ጃገማ ኬሎ እነ ዓለሙ ቂጤሳ ከበቀሉበት ከጅባትና ሜጫ:

 በቁርጥ ቀን የተገኘው  ፈይሳ ሌሊሳ  ዓለምን  አንጫጫ::

ፈይሳ ዘላለም ሊዘመርለት የሚገባ  ጀግና ነው:: ጀግንነት ምንድን ነው? የጀግንነት መለኪያውስ ምንድን ነው ? አያሌ ጀግኖች  ከጦር ሜዳ ይፈጠራሉ::  ጠላቱን የገደለ: ድል ያስገኘ በጠላቱ ላይ የበላይ የሆነ ሰው  ጀግና ተብሎ ይሸለማል:: ኒሻን ይጠለቅለታል::

ጀግንነት  በጦር ሜዳ ብቻም አይደለም:: የወገኑን ሕይወት ከሞት በማትረፍም ጀግንነት አለ :: ለአገሩ ክብር እና ለአገሩ መልካም ነገርን ለመፈጸም ሲል የሚገኝ ጀግንነትም አለ:: ሁሉም ጀግንነቶች ማዕረግ አላቸው::  ሹመት አላቸው:: ብሔራዊ ጀግና ተብለው ይሞከሳሉ:: ይወደሳሉ :: የፈይሳ ግን ላቅ ብሎ ዓለም አቀፋዊ ጀግንነትን ነው:: የፈጸመው ዓለም አቀፋዊ ድልን ነው :: ያስመዘገበው ዓለም አቀፋዊ ታሪክ ነው የሠራው:: ለዚህም ነው የኢንተርናሽናል ኮሚቴ  ደንቤን ተላልፈሃልና በኦሊምፒክ ሕግ መሠረት ሊቅጣህ ያላለው:: በዚህም ሌላ ድል ነው የተገኘው::

ፈይሳ ነጻነት ምን ያህል እንደሚያስፈልግ ነው አበክሮ ያስረዳው:: ያለነጻነት መኖር ኑሮ እንዳልሆነም ፈይሳ አረጋገጠ:: የፈይሳ ተጋድሎ አኩርቶናል::ነፍሱን ይማረውና የቬይትናምን ጦርነት በመቃወሙ የተዋቂውን የመሀመድ አሊን የሲድኒ ጀብድም አስታወሰን:: ምንም እንኩዋን በወቅቱ ብዙ ውግዘት ቢወርድበትም በአጭሩ ከተማረ የተመራመረ  ብሎ አልፎታል::

እንደ እኛ አገር ስንት ሺህ ምሁር ከአገሩና ከሕዝቡ በፊት የግሉን ጥቅም ባስቀደመበት ዘመን የፈይሳ ሌሊሳ ከአገርና ከሕዝብ በፊት የሚቀድም ጥቅም በአፍንጫዬ ይውጣ  ማለት ከዚህ በላይ ታሪክ ሠሪነት አለ?  ዘመን የማይሽረው ገድል ይሉሃል ይኼ ነው::

ዛሬ ወያኔዎች ያሉበት ሁኔታ ለጠላቴም አይስጠው የሚያስብል ነው:: የሚረግጡት መሬትና የሚጨብጡት  እንጨት  አጥተዋል:: ግራ ገብቶአቸዋል::  በጨለማ መርፌ መፈለግን ይዘዋል :: ተደናግጠዋል:: ተደነጋግረዋል:: ሥርዓታቸውን ለመጠገን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማወቅ ተስኖአቸዋል:: መፍትሄ በያዙት አጠናክሮ መቀጠልን ተያይዘዋል:: ይህ ደግሞ ያልታሰበ  ሳይሆን የታሰበ ውድቀትን ይጋብዛቸዋል:: ወያኔ ወደዚሁ ግብዣ እየገሰገሰ ነው::

ጀግናው አትሌት ፈይሳ ሌሊሳ  ከሚወድቀው ወዳቂ ጋራ ላለመውደቅ:  ከዲያብሎሳዊ አገዛዝ ጋራ ላለመገዝገዝ   በ26ዓመቱ ዘመንን ተሻግሮ የሚሄድ ረጅም ታሪክ  ሠራ::

ሃምሳ ቢወለድ ሃምሳ ነው ጉዱ

እንደፈይሳ ሌሊሳ ይበቃል አንዱ

በመጨረሻ ከፈይሳ ጎን ለመሆን የተደረገው እና እየተደረገ ያለው ሁለንተናዊ ርብርብ  የሚያኮራ ቢሆንም አንድ ነገር ለማስገንዘብ እገደዳለሁ::

ፈይሳን በተራ ደረጃ አይቶ ወደ አሜሪካ በአሳይለም ለማስመጣት ከሚደረገው ጥረት ይልቅ እንደ ኦሊምፒክ ጀግናነቱ ታይቶ  ከነሙሉ ክብሩ ለማስመጣት ቢሞከር የተሻለ ክብር ነው::

ይህ ደግሞ አዲስ አይደለም:: እንግሊዝ ካደረገችው መማር ይቻላል:: ዛሬ በኦሎምፒክ አደባባይ የእንግሊዝን ባንድራ የሚያውለበልቡ ማራቶኒስቶች እንግሊዛዊያን አይደሉም:: ብሶት ከአገራቸው ያስወጣቸው ናቸው:: እናም ይታሰብበት እላለሁ::

ክብር ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለኢትዮጵያ ብለው ለሚሰው ጀግኖች ይሁን!!!

 

ዝማሬና ውዳሴ የሚገባቸው ጀግኖች