ወይ አብረን እንሳቅ ካልሆነም አብረን እናልቅስ! [ከይገርማል]

Laugh-or-cry-...-Bothበየአካባቢው እየተደረጉ ያሉት ጸረ-ወያኔ እንቅስቃሴወች ክልላዊ ባህሪ መያዝ ያሳሰባቸው ግለሰቦች የሰሞኑ የአማራ እንቅስቃሴ የኢትዮጵያውያን እንጅ የአማሮች መባል የለበትም ብለው ሲከራከሩ እየተደመጡ ነው:: ከኢትዮጵያዊነት ደረጃው ዝቅ ብሎ የማያውቀው አማራ ዛሬ ላይ በአካባቢው የታጠረ የሚመስል ትግል እያደረገ መሆኑ ግልጽ ነው:: “ወልቃይት የአማራ ነው! በአማራ ላይ ያነጣጠረ የዘር ምንጠራ ይቁም! የወያኔ የበላይነት ይብቃ!—” እያለ ድምጹን ከፍ አድርጎ መፈክር እያሰማ ነው:: ይህን እንዲል ያስገደደው በራሱ ላይ ያነጣጠረ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ስለተከፈተበት እንደሆነ በበኩሌ እረዳለሁ:: በህልውናው ላይ የተጀመረውን የጥፋት ዘመቻ ለመመከት ደፋ ቀና እያለ ያለው አማራ የሌሎች ወገኖቹ ህይወት አሳስቦት በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎች የሚፈጸመውን የወያኔ የዕብሪት ጭፍጨፋ እያወገዘ ኢትዮጵያዊነቱን ማስመስከሩም አልቀረም::

የአማራውን ትግል ፍጹም ኢትዮጵያዊ መልክ ለመስጠት የሚደረገው ሙከራ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን እንደሚችል መገንዘብ ተገቢ ነው:: የአማራው ትግል በሀገራችን እንደቅንጦት የሚታዩት የዴሞክራሲያዊ መብቶች ይከበሩ በማለት የሚደረግ ትግል ሳይሆን ከወያኔ የዘር ማጥፋት ዕቅድ ለማምለጥ የሚደረግ የሞት ሽረት ትግል ነው:: አማሮች በሰላም ከሚኖሩበት አካባቢ እየተለቀሙ ሲታረዱ አንድም ክልል ሀዘናቸውን የተጋራ: የተቃውሞ ድምጹን ያሰማ አልነበረም:: ወደፊት ጊዜ ፍንትው አድርጎ የሚያወጣው ሀቅ የሚጠበቅ ሆኖ አሁን ባለን ግርድፍ መረጃ መሰረት በግላጭ ከተገደሉት በተጨማሪ ሦስት ሚሊዮን ያህል አማራ ያርግ ወይ ይስረግ ሳይታወቅ ዳብዛው ጠፍቶ ቀርቷል:: ይህንን አማራ-ተኮር እልቂት ሲያቀነባብሩ ከነበሩት ወያኔወች ጎን በመሰለፍ የአማራ ወኪል ነኝ የሚለውን ብአዴንን ጨምሮ ሁሉም ክልሎች በአማሮች ላይ የተለያየ የግፍ አይነት ፈጽመዋል:: ዛሬ ላይ እኒህ የጥፋት ሰለባ የሆኑት መከረኞች እየደረሰባቸው ያለው የዘር ማጽዳት ዘመቻ እንዲገታ ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ ናቸው:: ከእኛ የሚጠበቀው የእነዚህ ወገኖቻችንን ስሜት ተጋርተን ጩኸታቸውን አብረን እየጮህን በደላቸው እንዲሰማ የድርሻችንን ማበርከት እንጅ በጥቃት ስሜት እየተንተከተከ ያለውን የሕዝብ እንቅስቃሴ የሚያጠፋ ቀዝቃዛ ውሀ መቸለስ አይደለም::

ኢትዮጵያን ከወያኔ የጭቆና አገዛዝ ነጻ ለማድረግ የሚደረገው ግብግብ በአማሮች ላይ ብቻ የተጣለ ሸክም እንዲሆን የማይፈቅዱ አማሮች መኖራቸውን አምነን መቀበል ከስህተት ያድነናል:: ስለዚህ መተያየት እንዳይፈጠርና ወደኋላ ማለትን እንዳያስከትል በሚተላለፉት መልእክቶች ላይ ጥንቃቄ ሊደረግ ተገቢ ነው:: የሚሻለው: እንቅስቃሴ በማይታይባቸው አካባቢወች የጸረ-ወያኔው የአመጽ እንቅስቃሴ እንዲጀመር አመቻችቶ ሀገራዊ ገጽታ እንዲላበስ የተቀናጀ ትግል ለማድረግ መጣር ነው::

እንደሚገመተው ከሆነ ዛሬ ላይ የሕዝባቸው ሰቆቃ ያንገፈገፋቸው  በብአዴን ውስጥ ያሉ የአማራ ልጆች ከወገናቸው ጋር መስዋእትነትን ለመቀበል ወስነው በጽናት እንደቆሙ ነው:: እኒያ የወያኔን የጥፋት አላማ በአማራ ላይ ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ የነበሩት የቀድሞ የብአዴን አመራሮች ከታች እየተሳቡ በወጡ እውነተኛ የአማራ ልጆች የተተኩ መሆኑን የሚያሳይ የተግባር እንቅስቃሴ እንዳለ ለመገንዘብ አያዳግትም::

በአማራ ላይ የሚፈጸመው ሰቆቃ ያብቃ ብላችሁ የሕዝባችሁን የትግል እንቅስቃሴ ደግፋችሁ እየታገላችሁ ያላችሁ እናንተ የአማራ ልጆች ብርቱ ጥንቃቄ ልታደርጉ ይገባል:: ወያኔወች በክፋትና በተንኮል የተራቀቁ ናቸው:: ሌት ከቀን የሚያስቡት ጠላት ነው ብለው የፈረጁትን አማራ ከማጥፋት ጎን ለጎን የሕዝቡን አንድነት ሸርሽረው የተቃውሞውን እንቅስቃሴ ማርገብና ለማይጠረቃ የንዋይ ፍላጎታቸው ለብዝበዛ የተመቸ ሜዳ መፍጠር ነው:: የሚደክሙት ለዳር ድንበር መከበርና ለሀገር ብልጽግና: ለህዝብ ሰላም: ፍቅርና አንድነት አይደለም:: እነርሱን የሚያሳስባቸው  ከፈረሹበት የእርዝቅ መንበር ላይ የሚቀመጥ የልጅ ልጅ ተክተው ትግራይ-መር ኢትዮጵያን ለማስቀጠል ምን እናድርግ የሚለው ጥያቄ ብቻ ነው::

ይህን እነርሱ በጎ የሚሉትን አላማቸውን ለማደናቀፍ የሚነሳን ማንኛውም አካል ከማጥፋት ወደኋላ አይሉም:: ቂመኞች በመሆናቸው ይቅርታን አያውቁም:: ሽንፈትን አምኖ እንደ እንግዳ ዶሮ አንገትን ቀብሮ ከነርሱ ስር ማደር ከመጠቃት አያድንም:: በህይወት ላሉ አማራወች ይቅርና ለሞቱ አባቶቻችን ያልተኙ መርዘኞች መሆናቸውን ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት አያስፈልግም:: የሚሻለው “ከውርደት ሕይወት-የኩራት ሞት!” ይመረጣል ብሎ ከህዝብ ጎን ተሰልፎ እስከመጨረሻው ድረስ እየተፋለሙ ጥሎ መውደቅ ነው:: ነካክቶ ማፈግፈግ የረባ ነገር ሳይሰሩ ቀስ በቀስ ከምድረገጽ መጥፋትን ያስከትላል:: የሚያሸንፉን አንድ ሆነው በአንድ ልብ ስለተሰለፉ እንጅ በምናቸውም ከእኛ ስለሚበልጡ አይደለም:: ልብ አድርጉ! ይህንን የተነቃቃ የህዝብ ትግል እንዲበርድ አድርጎ ማፈግፈጉ ጉዳቱ ቀላል አይሆንም:: በቅንጅት አመራሮች የተሳሳተ አካሄድ የሕዝባችን የትግል መንፈስ የተቀዛቀዘበት ሁኔታ ተከስቶ እንደነበር ማንም አይስተውም:: አሁን ገንፍሎ እየወጣ ያለውን የሕዝብ አመጽ በአግባቡ ካልተጠቀምንበት ጭራሹኑ የተሰበረ መንፈስ ፈጥሮ ዳግም ይህን እድል የማናገኝበት ሁኔታ ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ተገቢ ነው::

ትግሉን ለማቀላጠፍ ዝግጁ ሆኖ መጠበቅ ኋላ ላይ ከመደናበር ያድናል:: ለዚያም ነው እስከቀበሌ ድረስ ወርዶ ሕዝብን የማንቃት: የማደራጀትና የማስታጠቅ ስራ ለይደር የሚተው የማይሆነው::  ስለሀገር አንድነትና ስለሕዝብ ነጻነት የሚጨነቁ ግለሰቦችና ፓርቲወች ድጋፋቸውን እንዲያበረክቱ ለማስቻል በራችሁን ብትከፍቱ የተሻለ ነገር አቅዶ ለመተግበር ይጠቅማል:: እናንተ ለማስተባበር ከቆረጣችሁ ጥሎ ለመውደቅ ፈክሮ የሚነሳው አማራ ድፍን ኢትዮጵያን እንደጉድ ማጥለቅለቁ የማይቀር ነው:: ይህን ለማድረግ ስትነሱ በቅድሚያ ከመሀላችሁ ተሰግስገው ለወያኔ አይንና ጆሮ ሆነው እየሰሩ ያሉትን ባንዳወች በማጽዳት መሆን አለበት::

አማራ ሲፈጥረው በሞራል የተገነባ ሕዝብ ነው:: ከሌላ አካባቢ መጥተው ተመሳስለው ለሚኖሩ ሰዎች ያለው ፍቅርና ክብር የተለየ ነው:: በሆነ ምክንያት ከሌላ አካባቢ ከመጡት ሰዎች ጋር የተጋጨ ያገር ሰው ቢኖር ይወቀሳል:: “የሰው አገር ሰው እንዴት ለማስቀየም ደፈርህ? ከወዳጅ ከዘመድ ርቆ እኛን አምኖ እኛኑ ዘመድ አድርጎ ተጠግቶ የሚኖርን ሰው ማስቀየም ደግ ነው?” ተብሎ ውግዘት ይደርስበታል:: በዚህም የተነሳ በአማራ ክልል የሚኖሩ የሌሎች ክልሎች ኗሪወችም ሆኑ የውጭ ሀገር ሰዎች ከአካባቢው ተወላጅ በተሻለ ሁኔታ ያለሀሳብ ተከብረው በሰላም ይኖራሉ:: ይሁንና “ያልበደለ ሰው ለምን ይቀጣል!” የሚሉ ተቆጭ ሽማግሌወች በሌሉባቸው አካባቢ የሚኖሩ ዘረኞች ከሌላ አካባቢ የመጡ ናቸው በሚሏቸው ምንም ጥፋት በሌላቸው ሰላማዊ አማራወች ላይ አማራ በመሆናቸው ብቻ ሀብታቸውን ይዘርፏቸዋል: ያፈናቅሏቸዋል: አስረው ያሰቃይዋቸዋል: ይገድሏቸዋል:: ይህን ከሞራልና ከሐይማኖታዊ ባህሪይ ያፈነገጠ ወንጀል ሲሰሩ ጠያቂ ሕግ: ወቃሽ ህሊናም ሆነ የሚፈሩት አምላክ የላቸውም:: እንዲህ ያለውን የሕዝብ ሰቆቃ ማስቆም የሚቻለው አንገትን ደፍቶ በመኖር ሳይሆን ግንባር ለግንባር ገጥሞ በመፋለም ነው::

አማራው ከአማራ ክልል ውጭ ሲኖር በየትኛውም ደረጃ በፖለቲካ አመራርነት መሰየም ቀርቶ የግልም ሆነ የሲቭል ስራውን በሰላም ሰርቶ መኖር አልፈቀድለት ብሎ ፍዳ ሲያይ ኖሯል:: በሌላ በኩል በአማራ ክልል የሚኖሩ የሌላ ክልል ተወላጆች በክልሉ የፖለቲካ ሀላፊነት ሳይቀር ከታች እስከላይ ድረስ ተሰግስገው ያለሀሳብ እየፈረዱ እያስፈረዱ ተቀምጠዋል:: በግል ስራ የሚተዳደሩትም ቢሆኑ ከኗሪው በላይ ሆነው ስለያንዳንዱ ግለሰብ መረጃ በማቀበል ሲያሳፍኑና ሲያስገድሉ እስካሁን ድረስ ዘልቀዋል:: በዚህ የተዛባ ተግባራቸው ለማፈር ያልታደሉት እኒህ ሰዎች ይባስ ብለው በአንድ ድምጽ “አህያ: ደደብ: የማይመጥኑ—” ናቸው ብለው የአማሮችን ተግባርና ባህሪ የማይገልጽ የስድብ ስም ሰጥተው አማሮችን በማንቋሸሽ እየጠሯቸው ነው:: ከአሁን በኋላ አማራው ግፍ ተሸክሞ አህያ የሚባልበት የትግሬ ወያኔወች የሀገር ሀብት እየዘረፉ ብልጥ የሚባሉበት ጊዜ ያበቃል:: ቢችሉ ከብልጥነት ወጥተው ብልህ ለመሆን ቢሞክሩ በዋናነት ለራሳቸው ይጠቅማቸዋል::

አማራ ማንንም በክፉ የሚያይ ሕዝብ አይደለም:: ሌላውም እንደራሱ የሚያስብ መስሎት ለረጅም ጊዜ ለመከራ ተጋልጦ ቆይቷል:: “ሞኝ የዕለቱን ብልህ ያመቱን” እንዲሉ አማሮች የዘላለም ህይወት ለመታደል ለህሊና የማይቆረቁር በፈጣሪ ዘንድ የተወደደ ተግባር በመፈጸም ታጋሽነታቸውን ሲያሳዩ የትግሬ ወያኔወች ግን የአፍታ ህይወት አጓጉቷቸው: ትዕቢት ልቦናቸውን ሰውሮት ከህዝብ ቀምተው ህዝብን እያዋረዱ ጥለውት የሚሄዱት ሀብት ያከማቻሉ:: ከእንግዲህ በኋላ ግን ሁኔታወች መስተካከል ይኖርባቸዋል:: ከቀን ቀን ይማራል የማይባልን አጥፊ ሰው አዝሎ እሹሩሩ ማለት ጉዳት እንጅ ጥቅም የለውም:: አማሮች አሁንም ቢሆን ባለጌወችን ፈርተው ሳይሆን አምላክን ስለሚያስቡ መሰረታዊ ባህሪያቸውን ቀይረው ማንንም ለማጥፋት ወይም ለመበቀል የሚነሱ አይሆንም:: ነገር ግን ከእንግዲህ በኋላ የትግሬ ወያኔወች ከመሀላቸው ዘና ብለው ተቀምጠው መረጃ እያቀበሉ ትግሉን እንዲያከሽፉ: ጭቆናን እንዲያስቀጥሉ  ሊፈቀድላቸው አይገባም:: ” የሰው ሞኝ የለውም ብልሀቱ ይለያያል እንጅ!” አይደል የሚባለው? እኛም እንዳቅማችን ብልሀት አናጣም:: ሰላማዊ ኗሪ መስለውም ሆነ በግላጭ የጦር መሳሪያ ታጥቀው የወያኔ የመረጃና የአፋኝ ኃይል ሆነው የሚሰሩ በክልሉ የሚኖሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ባስቸኳይ ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ይደረግ:: ይህን የሕዝቡን ትግል ለማኮላሸት የተሰገሰገን የጥፋት ኃይል በጉያ ታቅፎ ይዞ ታግለን እናሸንፋለን ማለት ከየዋህነት የዘለለ ሞኝነት ነው:: ይህ የዘረኝነት ጉዳይ አይደለም: መተኪያ የሌለው የትግል ስትራቴጅ እንጅ::

አማሮች አሁንም ኢትዮጵያን ይወዳሉ:: አሁንም የህዝብን በሰላም አብሮ መኖር ይፈልጋሉ:: አይደለም በአንድ ሀገርና በአንድ ሰንደቅ አላማ ስር ክፉና ደጉን ተጋርተው አብረውት ለኖሩ ሕዝቦች ይቅርና ከሌላ ሀገር ለመጣ ሰላማዊ ሰውም ቢሆን ፍቅርና ክብር የሚሰጥ ትሁትና ፈሪሀ-እግዚአብሔር ያደረበት ሕዝብ ነው: አማራ:: ሰላም የሚነሱት ወያኔወች በያዙት መንገድ እስከቀጠሉ ድረስ ግን “ለሰላም ስትሉ ሁሉንም ነገር ተውት” ማለት “በወያኔ የሚደርስባችሁን ግፍ ችላችሁ አንገታችሁን ደፍታችሁ ተቀመጡ” ማለት ነው:: ከእንግዲህ በኋላ በሀገር ልጅነት ስም ነጻነታቸውን ተገፈው በባርነት ለመኖር አይፈቅዱም:: በዚህ ምክንያት የሚደፈርስ ሰላም ካለ መደፍረሱ የግድ ይሆናል:: ሰላም በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሚመጣ አይደለም::

ካድሬወቹን በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን እያቀረበ “ጥያቄ ካለ በሰላማዊ መንገድ መጠየቅ ሲቻል ለአመጽ መነሳሳት አግባብ አይደለም” የሚል የማጭበርበሪያ አስተያየት የሚያሰጠው ወያኔ ከስህተቱ ቢማር ይበጀዋል:: ለሕዝብ ጥያቄ ጆሮ ሰጥቶ የሕዝቡን ፍላጎት ተከትሎ የሚሰራ ቢሆን ኖሮ አሁን እየታየ ያለው አመጽና ውድመት ባልተከሰተም ነበር:: በየአካባቢው የሚደረጉት እንቅስቃሴወች በሙሉ የሕዝብን ጥያቄ አዳምጦ ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት ባለመኖሩ የተፈጠሩ መሆኑን ማንም አይስተውም:: ሰላማዊ በሆነ መንገድ የሕዝብን ጥያቄ ያቀረቡ የሕዝብ ወኪሎች በእብሪት ስለታፈኑ ነው ተቃውሞው የተቀሰቀሰው::

የትግራይ ሕዝብ “ጥሩውን ጥሩ: መጥፎውን መጥፎ” ማለት ማወቅ አለበት:: ከዚያም አልፎ ጥሩውን በመደገፍ መጥፎውን ደግሞ በማውገዝ ከሌሎች ሕዝቦች ጎን ተሰልፎ አጋርነቱን መግለጽና መስዋእትነት መክፈል ይኖርበታል:: ያ ሲሆን ነው መተሳሰብ አለ ማለት የሚቻለው::

 

ኢትዮጵያውያን ክፉውንና ደጉን ተጋርተን አብረን ኖረናል:: ዛሬም ያንኑ ልማዳችንን ሳንቀይር እንደወቅታዊ ሁኔታው ወይ አብረን እንስቃለን ወይም አብረን እናለቅሳለን:: አንዳችን እየሳቅን ሌላችን የምናለቅስበት አግባብ ግን ሊኖር አይችልም::

ትንሳኤ ለኢትዮጵያ!

ወይ አብረን እንሳቅ ካልሆነም አብረን እናልቅስ! [ከይገርማል]