አሜሪካ፡ “ህወሃት አብቅቶለታል”

የታቀደ፣ ግን ድንገተኛ የሚባል መፈንቅለ መንግሥት ይጠበቃል

በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ

army-in-addis-e1472451071352-620x310በኢትዮጵያ የስርዓት ለውጥ እንዲካሄድ የማይፈልጉት የአሜሪካ ባለስልጣናት ህወሃት አገር መምራት የማይችልበት ደረጃ ደርሷል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። የሚያደርጉትን ቢያውቁም ለመፍትሄ በተናጠል ተቀናቃኝ ፓርቲዎችንና የሲቪክ ማህበራትን “ምክር” እየጠየቁ ነው። አሁን ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ በዚህ ከቀጠለ ኢትዮጵያን ላለማጣት ድንገተኛ የሚመስል ግን የታቀደ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ሊደረግ እንደሚችልም ፍንጭ እየተሰጠ ነው።

የጎልጉል ታማኝ መረጃ ሰዎች እንዳሉት የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግምባር (ህወሃት) እንዳበቃለት የገመገሙት የአሜሪካ ባለስልጣናት “ከወዲሁ አንድ ነገር ማድረግ አለብን” የሚል አቋም ከያዙ ሰነባብተዋል። ለዚሁም መነሻቸው ህወሃት መልሶ እንዲያገግም ሊረዱት አለመቻላቸውና ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የኢትዮጵያን መክሰር አለመፈለጋቸው ነው።

“ህወሃት አገር መምራት ካቃተው፣ ኢትዮጵያን ላለማጣት ምን ማድረግ አለብን” ከሚለው መሰረታዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ዝንባሌያቸው በመነሳት አሜሪካኖቹ በየእርከኑ አገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የተቀናቃኝ ፓርቲ መሪዎችን፣ ነፍጥ አንስተው ከሚታገሉ፣ በውጭ አገር ከሚገኙ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ከሲቪክ ተቋማት ጋር ውይይት እያካሄዱ ነው። ውይይቱ “ምን እናድርግ በሚል ምክር የመጠየቅ አይነት ነው” ሲሉ የመረጃው ባለቤቶች ያስረዳሉ። አሜሪካኖች የሚያድርጉትን እያወቁ ምክር የመጠየቃቸውን ጉዳይ የመረጃ ምንጮቹ ባያጣጥሉትም ምክር ተጠያቂዎቹ ተደራጅተውና ህብረት ፈጥረው ተጽዕኖ መፍጠር የሚችሉበትን ሁኔታ ሊያስቡበት እንደሚገባ ይመክራሉ።

(ከዚህ ዜና ጋር በተያያዘ እነ አባይ ጸሃዬ “አማራና ኦሮሞ ተባበሩብን፤ ሰግተናል” በሚል ርዕስ ጎልጉል በዘገበበት ዜና ላይ አሜሪካ ህወሃትን ለማዳን ጥገናዊ ለውጥ እንዲደረግ መፈለጓን፤ ለዚህም በተናጠል የተቃዋሚ ቡድኖችን እያናገረች መሆኗን ጠቅሰን ነበር)

kerryቴድሮስ አድሃኖም የሌሉበትና ህወሃት/ኢህኣዴግ የታገደበት ስብሰባ በጆን ኬሪ ሲመራ – ከጎናቸው የኬንያዋ ውጭ ጉዳይ ሚ/ር አሚና ሞሐመድ ቀጥሎ የኡጋንዳው (ምስላቸው አይታይም) በግራ የመጀመሪያው የድቡብ ሱዳኑ ዴንግ አሎር ቀጥሎ የሶማሊያው አብዲሳላን ኦማር ቀጥሎ የሱዳኑ ኢብራሂም ጋንዱር Photo – PAN SIWEI

በደም የተነከረውና ህዝባዊ ቁጣ የናጠውን ህወሃት አቅፋና ደግፋ ወደ ዙፋን ያመጣችው፣ በጀት ቆጥራ ስንዴ ሰፍራ እየደጎመች ዙፋኑን ያጠበቀችለት፣ ሲገድል ከበሮ የደለቀችለት፣ የሕዝብ ድምጽ ዘርፎ ራሱን ሲሾም “ዴሞክራሲያዊ” ያለችው፣ ከህዝባዊ ማዕበልና ከውስጥ መበላላት ያተረፈችው፣ የዛሬውንም ህዝባዊ ማዕበል በጥገና እንዲሻገር ስትደክምለት የኖረችው አሜሪካ አሁን ተስፋዋ እንደተመናመነ ለማወቅ ተችሏል። ይህንኑ ሃሳብ ለማጠናከር ሰሞኑን ኬንያ የተደረገውን የጸጥታ ጉዳይ ስብሰባ ለአብነት ያነሳሉ።

ባለፈው ረቡዕ ኬንያ የተደረገውና የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጆን ኬሪ የመሩት የጸጥታ ጉዳይና የጸረአሸባሪነት ስብሰባ ከአራት ወራት በፊት ሲታቀድ ለጉባኤው የተመረጠችው አገር ኢትዮጵያ ነበረች። ስብሰባው ህወሃት በደረሰበት ህዝባዊ አመጽ አማካይነት ወደ ኬንያ መዛወሩ ብቻ ሳይሆን ስለ አልሻባብና ቦኮ ሃራም ውይይት በተደረገበት ስብሰባ ላይ ኬሪ አንድም ጊዜ የኢትዮጵያን ስም አለማንሳታቸው በይፋ ታይቷል፡፡ “በዲፕሎማሲው ቋንቋ ይህ የሚያሳየው አሜሪካ ለህወሃት ጀርባዋን መስጠት መጀመሯን ነው” በማለት የምስራቅ አፍሪካን ፖለቲካ የሚናገሩ ያስረዳሉ። ሲያክሉም ኬሪ ይህ ሁሉ ደም በሚፈስበትና ህዝብ በጅምላ በሚታሰርበት አገር ተገኝተው ስለ ጸጥታ ጉዳይ ስብሰባ ማድረጋቸው አሜሪካንን የሚያሳፍር ከመሆን ባሻገር አለቃቸው ፕሬዚዳንት ኦባማ “ዴሞክራሲያዊት” ብለው ባሞገሷት አገር ላይ ስለ ህወሃት ደምአፍሳሽነት ከዓለምአቀፍ ጋዜጠኞች ጥያቄ ቢቀርብላቸው የአሜሪካንን ኪሣራ አምኖ ላለመቀበል የተቀነባበረ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህም ስለ አልሻባብ እና ስለ ደቡብ ሱዳን ደኅንነት በተጠራው ስብሰባ ላይ “የሶማሊያ መሃንዲስ የአልሻባብ ባለገድል” እንዲሁም የደቡብ ሱዳን “አሸማጋይ” የሆነውን ህወሃት እንዳይገባ ተከልክሏል፡፡

መለስ በG-20 ስብሰባ

መለስ በG-20 ስብሰባ

የምዕራብ ተላላኪ የነበሩት ሟቹ “ባለራዕይ” መለስ በአገር ውስጥ ያለው ግፍ እያሳጣቸው በመጣ ጊዜ ጌቶቻቸው ጀርባ ሰጥተዋቸው የዕራት ግብዣ ጠረጴዛ ላይ ሻማ ያዥ አሽከር መስለው የታዩበት ጊዜ የሚታወስ ነው፡፡

በ1983 የሎንዶን ድርድር ኢትዮጵያን በኸርማን ኮኽን አማካይነት ለህወሃት ያስረከበችው አሜሪካ “ህወሃት አብቅቶለታል” ከሚለው ድምዳሜ ላይ ባለችበት ባሁኑ ሰዓት የተቃዋሚው ኃይል በቶሎ አገር ወደማዳን አጀንዳ በኅብረት ተንቀሳቅሶ አንድ ደረጃ ላይ ካልደረሰ አሜሪካ ድንገተኛ የሚመስል ግን አስቀድሞ የታቀደ ወታደራዊ የመፈንቅለ መንግስት ልታካሂድ ትችላለች የሚል ግምት እንዳለ ለማወቅ ተችሏል። የዜናው ሰዎች እንደሚሉት ከሆነ አሜሪካ ይደረጋል ብላ የምትጠብቀው ኩዴታ “በድንገት የሚደረግና የማይታወቅ አይደለም” ሲሉ በየደረጃው ከተቀመጡት አማራጮች መካከል አንዱ ስለመሆኑ ፍንጭ ይሰጣሉ። ሲያብራሩም የቀድሞውን የህወሃት ታጋይ ጻድቃንን እና ሌሎች የቀድሞ የመከላከያ ኃላፊዎችን ከፊት ለፊት ያመጣሉ።

ሰሞኑን ጻድቃን ገ/ትንሣኤ ያቀረቡት “የመፍትሔ ሃሳብ” ውስጥ የመከላከያውና የደህንነቱ መዋቀር እንዳለ ቆይቶ ህገ መንግስቱን መሰረት ያደረገ የስርዓት ማሻሻያ ከማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ የሚያሳስብ ነው። ዜናውን ያቀበሉት ክፍሎች ሲያከሉም “በዚህ እሳቤ ውስጥ ሆኖ መፈንቅለ መንግስቱን ማስላት አግባብ ነው” ባይ ናቸው። እናም አሜሪካ በግል የምታናግራቸውና የኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ በቶሎ ግንዛቤያቸውን ሊያሰፉና የመፍትሄ ሃሳብ ሊያቀርቡ እንደሚገባቸው ያሳስባሉ።

ላለፉት 25 ዓመታት ታማኝ በሆናት ህወሃት አማካኝነት አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ የወታደራዊና የደኅንነት መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሷ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያን ላለማጣት የምትፈልገው ካላት ወታደራዊ ኢንቨስትመንትና ሌሎች ጥቅማጥቅሞች አኳያ እንደሆነ በሰፊው ይታመናል፡፡

ከተያዙት የተለያዩ መፍትሔዎች መካከል መፈንቅለ መንግስት አማራጭ ከሆነ “ሥልጣን እስከ ሞት” በሚሉ ህወሃቶችና ተራው የእኛ ነው በሚሉ “ንሰሃ በገቡ የለውጥ አራማጅ” ህወሃቶች መካከል እርስ በእርስ መበላላት ሊኖር እንደሚችል ከግምት በላይ ስጋት አለ። መከላከያውና ደህንነቱ የሚመራው ባንድ አካባቢ ተወላጆች መሆኑ የአቋም ልዩነት ከተነሳና መከዳዳት ከተከሰተ መቀዳደም ሊኖር እንደሚችል የሚገመቱ አሉ። በሌላ በኩል ከስልጣናቸው በላይ ዋስትና አግኝተው ያላቸውን ሃብት ማስተዳደርና መኖር የሚፈልጉ ስለሚበዙ ጉዳዩ እጅግ ቀላል የመሸጋገሪያ መንገድ እንደሆነ የሚያስቡም አሉ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ህዝባዊ ተቃውሞው ስልቱን እየቀያየረ ተጠናከሮ ቀጥሏል። ከየአካባቢው በምስል እየተደገፉ የሚወጡት መረጃዎች እንደሚያሳዩት ህዝብ እምቢተኛነቱን የሚገልጽበት መንገድ ኢኮኖሚውን እያመነዠገው ነው። ይህ በሆንበት ሁኔታ ህዝባዊ እምቢተኛነቱ ትምህርት ቤቶችና ከፍተኛ ተቋማት ሲከፈቱ ዋና ዋና ከተሞችን በሙሉ ያዳርሳል የሚል ፍርሃቻ ነግሷል።

በሌላ ዜና በአማራ ክልል የሚካሄደውን ህዝባዊ እምቢተኛነት አስመልከቶ መረጃ የሚሰጡ የፖለቲካ ድርጅቶች የመናበብና የመረጃ አሰጣጥ ስልት ችግር እንዳለባቸው ተሰምቷል። በብዛት አሜሪካ ራዲዮ የሚያናግራቸው እነዚህ ክፍሎች የሚሰጡትን መረጃ የማደራጀትና በየሰአቱ የማጎልበት ችግር ይስተዋልባቸዋል። እንደውም ጉዳዩን ወደ ህዝብ ወኪሎች ቢገፉት የተሻለ እንደሆነ የሚመከሩም አሉ። በቅንጅት ወቅት ሁሉም የተሳከረ መረጃ እየሰጡ የተፈጠረውን ችግር የሚያስታውሱ ክፍሎች መረጃ ተደራጀቶ የሚሰራጭበት አግባብ ሊፈለግ እንደሚገባ አበክረው ይመክራሉ። ሕዝባዊ ተቃውሞ አስቀድሞ ከጀመረው የኦሮሞ ተቃውሞ ጋር ኃይልን ማስተባበር እንደ አማራጭ ሊታይ ይገባዋል ሲሉ ሃሳብ ይሰጣሉ፡፡

ከበላይ አመራሩ በስተቀር አብዛኛው የብአዴን ካድሬ ከድቷል በሚባልበት ባሁኑ ወቅት “መንግሥት ፈርሷል” እየተባለ መነገሩና ሕዝቡ በጎበዝ አለቃ እየተመራ መምጣቱ ህወሃትን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ከቶታል፡፡ ሁሉም ድርጅቶች የተናጠል ስብሰባ አካሂደው በመጨረሻም የኢህአዴግን የሚያደርጉበት የተለመደ አሠራር ቀርቶ ህወሃት ብቻ ባደረገው ስብሰባ የኢህአዴግ ምክርቤት መግለጫ አውጥቷል፡፡ ይህም እንደ ኦህዴድ ብአዴንም የከዳና መተማመን በግምባሩ ውስጥ የመነመነ መሆኑን የሚያሳይ ሲሆን በቀጣይ ህወሃት በኦፊሴል ባያውጅም እንደ ኦሮሚያ የአማራን ክልልም በወታደራዊ አገዛዝ ሥር እንደሚያስተዳደር አመልካች ሆኗል፡፡

ይህ አካሄድ ለህወሃት የኅልውና ጉዳይ ስለሆነ የተከፈለው መስዋዕትነት ተከፍሎ “አገር በማዳን” ስም በበርካታ አካባቢዎች የከረረ ወታደራዊ እርምጃ ሊወስድ ይችላል የሚለው በስፋት የሚታመንበት ሆኗል፡፡ በአሜሪካ ድጋፍ ሲቪል መሰል ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተከሰተም አገር ማረጋጋት በሚል ተመሳሳይ እርምጃ የማይወሰድበት ምክንያት እንደሌለ አስተያየት ይሰጣል፡፡ በመሆኑም “ህወሃት አብቅቶለታል” በሚባልበት በአሁኑ ሰዓት የተቃዋሚው ኃይል ሁሉን አቀፍ አንድ ወጥ ቻርተር ወይም አጀንዳ መቅረጹ በቶሎ ሊሰራበት የሚገባ እንደሆነ ጉዳዩ የሚያሳስባቸው አበክረው ይናገራሉ፡፡ (ቀዳሚ ፎቶ አጋዚ በአዲስ አበባ ፎቶ ምንጭ AP)


 

አሜሪካ፡ “ህወሃት አብቅቶለታል”