የወያኔ ልኡካን የጎንደር ውሎ

Amhara protest in Gondar

ያሬድ አማረ

ከመጀመሪያ ጀምሮ የጦር ሀይል አማራጭን በመጠቀም ሽንፈትን ያስተናገደዉ ሕወሃት በዲፕሎማሲም ዳግም ተመልሶ ሊያገግም በማይችል ሁኔታ ዛሬ 27/12/2008 ጎንደር ከተማ ላይ ልኩ ተነግሮት በኪሳራ ተሸኝቷል። ሁሌም ቢሆን “የእኔ መንገድ ብቻ ትክክል ነው” በሚል ትእቢቱ የምናዉቀዉ ህወሃት አማራ ምድር ላይ የሚሄድበት እግሩ ከተቆረጠ ሰነባበተ። ፌደራል ፖሊስ ከአቅሜ በላይ ነዉ ብሎ ሪፖርት ካቀረበ ማግስት ጀምሮ በስርዓቱ የጦር ጠንሳሾች (አግአዚ) ተመርቶ ደም ማፍስስ ከጀመረ ሰነባበተ።

ትእቢተኛ በቆሎ ከጤፍ ሆድ ዱቄት እንዲወጣ አያዉቅምና ፍሊሚያዉ የአገዛዙን እድሜ እያሳጠረ መጥቶ የትግሉ የመጨረሻ ምእራፍ ደርሶል። አማራነትም ፈጽሞ ላይከስም እየጎመራ፣ እየተንዠረገገ፣ እየሰፋ እየገዘፈ መጥቷል። ከመከላከል ወደ ማጥቃት ተሸጋግሮል። ዛሬ በእለተ አርብ ነሃሴ 27 ጎንደር ከተማ ውስጥ ባሉ ሶስት ሰፋፊ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ላይ የህዋሃት ልኡካን ባለስልጣናት በጎንደር አማራ አማካኝነት መራር ዲፕሎማሲያዊ ሽንፈትን ተጎንጭተዋል።

ከኢህአዴግ ማእከላዊ ኮሚቴ ተመርጠዉ የተላኩ የህወሓት መልክተኞች በሶስት ጎራ በኩል ተመዳድበዉ ብሶተኛዉን ህዝብ ለማናገር በአዳራሾቹ ታድመዋል።

ምድብ 1- ከንቲባ ጽ/ቤት በሚገኘዉ አዳራሽ ዉስጥ የኮሚኒኬሽን ጉዳይ ሃላፊ ተብየው ወፈፌው ጌታቸዉ ረዳ፣ እንዲሁም የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጥላሁን ተሰይመዋል።

ምድብ 2- ሳይንስ አምባ በሚገኘዉ አዳራሽ ዉስጥ የክልሉ ፕሬዝደንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉ፣ እንዲሁም የግብርና ሚኒስተሩ አቶ ተፈራ ደርበዉ ተገኝተዋል።

ምድብ -3 ፒያሳ በሚገኘዉ ሲንማ አዳራሽ ዉስጥ የክልሉ የብአዴን የፖለቲካ ሀላፊዎች በብሶተኛዉ ተሰብሳቢ ፊት ተደቅነዋል።

ስብሰባዉ አረፋፍዶ ተጀመረ። በእለቱ የሀይማኖት አባቶች ደምቀዉ ዋለዋል። ከወትሮዉ በተለየ መልኩ ኮከብ ሆነዉ ለምሳ አጋማሽ ወጡ። እንዲህም ሲሉ ሞገቷቸዉ:-

“ከዚህ በሆላ መስቀል ጥላ እና ታቦት ይዘን የምንወጣዉ ወጣቱን እኛ ከፊት ሆነን ለማዋጋት እንጂ ለመሸምገል አይደለም። ከዛሬ በኋላ ድምጽ ማጉያችንን ይዘን የምንናገረዉ የእናንተን ዲስኩር ሳይሆን የልጆቻች ስሞታ ነዉ። ከእነሱ በፊት እኛን ያድርገን” ሲሉ የታወቁ የኦርቶዶክስ አባት ተናገሩ።

ቀጠሉ እና ሌላኛዉ ወንጌላዊ አባትም ከሙሴ የኦሪት መጽሀፍ ጠቅሰዉ “ርስትን የሚያፈልስ የተረገመ ነዉ” በማለት ህወሃቶች የተረገሙ መሆናቸውንና እግዚሃብሄር ስልጣናቸዉን ነጥቆ ለተተኪዉ ዳዊትን እንዳዘጋጀ ነገሩአቸዉ።

አንድ የታወቁ ሸህም “አሏህ ሁሌም ከተበዳዬች ጎን ነው የሚቆመው፣ አማራ እጅግ ተበድሏል እናም አሏህ ከእኛ ጋር ነው” ሲሉ በሃይል ተናገሩ።

ጌታቸዉ ረዳ አፉ ተሳስቶ የሚናገረው ጠፍቶት ሲቁለጨለጩ እና ሲደናበር ዉሏል።

የሌላው ምድብ የስብሰባሰው ተሳታፊዎች አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉን “ከ 35 ሚሊዩን በላይ ጀግና የአማራ ህዝብ ጋር ሆኖ የሚስፈራህ ምንድን ነዉ? ከጀግናዉ ኮሎኔል ደመቀ ታሪክ ጋር ሊያስደምር የሚችል እድል በእጁ ላይ ነው፣ ተጠቀምበት፣ የሕወሓት ሎሌነት ታሪክ አይሆንም፣ ለህዝብ ከወገንክ ህዝብ መከታ ይሆንሃል።” ብለውታል።

አቶ ገዱ በሚሰማው ነገር ስሜታዊ እንደነበረ ለመገንዘብ ተችሏል። ከዚህ በኋላ ለታሪክ እንዲኖር አበክረዉ ነግረውታል።

ከአቶ ገዱ ቀጥሎ ተራው የደረሰው የግብርና ሚኒስቴሩ የጎርጎራዉ ልጅ ተፈራ ነበር። 25 አመት ሚኒስቴር ነበርክ። እኛ በኩራዝ እና በሻማ ያስተማርነህ ለዚህ አልነበረም። ምነዉ ጄኔሬተሩ ወደ ትግራይ ሲሄድ እናንተዉ ባልመከታቸሁ ኑሮ? ታዲያ ዛሬ ምን ይዘህልን ነዉ የመጣህዉ? የቱሪስት መስህቧ የትዉልድ ከተማህ ጎርጎራ እንኳን ይኸዉ 25 አመት ከጎንደር የሚያገናኛት የ60 ኪሎ ሜትር አስፓልት አልተነጠፈላትም። ዛሬ ጦር ፍጅት ባወጀብን አለቃህ ትእዛዝ ልትፈጥም መምጣትህ አይበጅህም! ተመከር! ሲሉ በጥብቅ አስጠንቅቀውታል።
ብሶት የወለደዉ የአማራ ድምጽ በመጨረሻም ባለ 4 ነጥብ የአቋም መግለጫ አዉጥቷል።

1ኛ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የህወሀት የመከላከያ ሰራዊት ከአማራ ምድር በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ
2ኛ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ኮ/ል ደመቀ በአስቸኳይ እንዲፈታ
3ኛ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የታሰሩ የወልቃይት እና የጠገዴ ኮሚቴ አባላት በአስቸኳይ እንዲፈቱ
4ኛ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ወራሪዉ የወያኔ መንግሰት በአስቸኳይ ተከዜ ማዶ እንዲሻገር እና የራሱን ምድር እንዲያስተዳድር

ይህ ካልሆነ ግን ከቄስ እስከ ሸህ፣ ከወጣት እስከ ሽማግሌ፣ ሴት ወንድ ሳይል የአማራ ህዝብ በአንድ ላይ፣ በአንድ ልብ ነፃነቱን በደም መስዋዕትነት ያፀናል። ከዚህ በኋላ በሰላማዊ ሰልፍ የሚሞት አንድም የአማራ ነብስ አይኖርም ብለዋል።

Source Article from http://www.mereja.com/amharic/511930

የወያኔ ልኡካን የጎንደር ውሎ