ላይ ላዩን ሲታይ የአማራ ትግል ባለቤት የሌለው ይመስላል – ኄኖክ የሺጥላ

እንዲሁ ከውጭ ላይ ላዩን ሲታይ የአማራ ትግል ባለቤት የሌለው ይመስላል። ይህም ለ ትግል ዘራፊዎች ትልቅ ቀዳዳ የፈጠረ ይመስላል ። እኔ ግን ይህንን ጉዳይ የማይበት አይኔ የተለየ ነው ። የአማራን ልቦና የማያውቅ ፥ የአማራን መንፈስ እና ታሪክ የማያውቅ ፥ እርግጥ በአማራ ደም ከብሮ ፥ ትግሉ የኔ ነው ብሎ ፥ እንደለመደው ተብለጥልጦ ፥ በአማራ ደም ተንሳፎ ቤተ መንግስት ሊገባ ይመኝ ይሆናል ። ጥቂት ሆድ አደር አማራዎችን እየጋለበ ፥ ከፊት ለፊት እንደ መንጆ እስቀድሞ ፥ አማራ አልሶ ትግሬ ወይም ሌላ ሆኖ ሊመጣም ፈልጎ ይሆናል ። ይህ ሁሉ ግን አማራ ምን አይነት ህዝብ እንደሆነ የማያውቅ እንከፍ የሚመኘው ምኞት ከመሆን ውጭ ሌላ ምንም ሊሆን አይችልም። አማራ እንኳን የደሙን ፥ የሰው ደምን አሳልፎ አይሰጥም! አማራ ሲጥል እንጂ ሲታገል አይታይም ያለው ማን ነበር?
ለማንኛውም ውድ ወንድሞቼ እና ወዳጆቼ ፥ እነ እንቶኔ ትግሉ የኛ ነው ፥ አለንበት ፥ እና ወዘተ ቢሉ ከነሱ ጋ አትነታረኩ ። በኢትዮጵያ የትግል ታሪክ ሁሌም የፖለቲካ ቁሞ ቀሮች እና የውራ ተከታዮች ፥ ባገኙት አጋጣሚ ያደረ አፋሽ መሆን ስለመመኘታቸው አትዘንጉ ። በተቻለ መጠን ፥ ተውረግርገውም ሆነ ተንቀጥቅጠው ፥ በታችሉት አጋጣሚ ትግሉን ለመቀማት የተቻላቸውን ሊያደርጉ ይችላሉ ። እንደው ችለው ካደረጉት እሰየው ! የሚሆንላቸው ግን አይመስለኝም!
እኔ አማራን ሳውቀው ( ዘሮቼ ናቸውና የገባኝም የገባኝ ሁኜ ነውና) ፥ የሚሞተው አማራ ፥ ብረት የያዘው አማራ ፥ የሚታገለው አማራ ፥ ደሙ የአማራ ፥ የትግሉ ሜዳ በአማራ ህዝብ አፈር ላይ ሆኖ በምን አይነት መንገድ ነው እነ እንቶኔ ሊሰርቁት ወይም ሊቀሙት የሚችለው ። ይህ ራስን ካለመረዳት እና አማራን በቅጡ ካለማወቅ ይመነጫል ። ይልቅስ ሙከራቸው ባልበላውም ጭሬ ላፍሰው ከሚል ክሹፍ ማንነት የመነጨ ቢሆን እንጂ !

ትንናት በአርማጨኾ ማን እንደሞተ ፥ ማን ምን እንደሆነ የምናውቅ እናውቃለን ። ዛሬም ሳንጃ ሲካሄድ የዋለው ተኩስ ፥ ሰዎቹን በስም ብቻ ሳይሆን በአካልም እናውቃቸዋለን ። እኛ የፖለቲካ ግብ ግብ ውስጥ አንገባም ! የሚያስገባም ነገር የለም!

የምናውቀው እውነት በራሱ ብቻውን ግብ ግብ ውስጥ እንድንገባ የሚያደርገን አይደለም!

በአማራ ክልል የተነሳው አመፅ ምክንያቱ አማራነት ነው ። የማንነት ጥያቄ ነው ። ይህንን አምኖ የማይቀበል ማናቸውም አካል ፥ የትግሉ ጠንሳሽ አይደለም አካል ለመሆን እንዴት ይቻለዋል?

እኛ የአማራ ክልል ነዋሪዎች ሳንሆን የአማራ ህዝቦች ነን ። ይህንን ማንሻፈፍ አማራነታችንን አያንሻፍፈውም ! አማራ ኩሩ ህዝብ ነው ፥ ቆራጥ ህዝብ ነው ፥ ጀግና ህዝብ ነው ። የማንንም እርዳታ ሳይሻ አማራ ራሱን በራሱ ነፃ ማውጣት የሚችል ህዝብ ነው ። ጀግናው ኮ/ል ደመቀ፥ በታሪካዊ ማንነቱ ላይ የተቃጣበተን የታሪክ እና የሃገር ቅሚያ ለማስቆም ባደረገው ትግል የመጀመሪያውን አብሪ ጥይት ተኩሷል። ይህንን እኛ ነን የጠነሰስነው ቢሉ ከመሳቂያነት አያልፉም ! በመሰረቱ በአማራ ማንነት የማያምን እና የዚህ ማንነት አካል ያልሆነ እንዴት የዚህ ( የአማራ ማለቴ ነው ) ትግል ጠንሳሽ ሊሆን ይችላል ? በየት በኩል ? አማራ ባሪያ አይደለም ፥ ወደፊትም አይሆንም! አማራ አቅመ ቢስ ህዝብ አይደለም ፥ ስለዚህ ውጊያ ከማያውቁት ጦርነት አይማርም! አማራ ሰነፍ ህዝብ አይደለም ፥ የሚሆነውን ያውቃል ፥ አረማመዱን ያውቃል ። ታግሎ ማሸነፍ ለአማራ ብርቅ አይደለም ። ሲታገሉ መሞት ለአማራ አዲስ ነገር አይደለም ። የአማራ ታሪክ እኩሌታው ጀብድ ፥ እኩሌታው ድል ነው ! ያንን የማያውቅ ፥ አማራን እያታገልኩ ነው ሊል ይችላል ። አለ ማለት ሆነ ማለት ግን አይደለም ። የማይሆነው ደሞ ሰለማይሆን ነው! የማይሆነው እየሆነ ያለውን ስለምንረዳ ነው ! የአማራ ትግል ቀሽሞች በአቦሰጥ ከገቡበት የፖለቲካ ቅርቃር ውስጥ መሽሎኪያ እና መውጫ ቀዳዳ ሊሆን አይችልም ! የማይችለው ደሞ ስለማይሆን ነው! ውሳኔ እይደለም ፥ እውነት እንጂ !

የግርጌ ማስታወሻ

እርግጥ የተደራጀን አንመስልም ። በመርህም እናምን ይሆናል ። ለነገሩ መርህ ምን ይሰራል ። በመርህ ከመዝረፍ ያለ መርህ ሃቀኛ እና የህዝብ ልጅ መሆን ይልቃል ።
ድርጅት የለንም ። ግን መንፈሳችን ድርጅት ነው ። እርምጃችን ከባተሌ ስብስቦች የላቀ እና የረቀቀም ነው ። አርማ እና ማህተም አዘጋጅተን ፥ ቢሮ ከፍተን አርባ አመት አላዛጋንም ። ምክንያቱም ስራ ለመስራት በራሳችን ማሰብ እንጂ አሳሳቢ አካል ስለማንሻ! ማህተሙ እና ቢሮው ሳይሆን ሃሳብ እንደሆነ ስራ የሚሰራው ስለሚገባን ። ተጋባዥ ተናጋሪ ፥ ደስኳሪ እና አውሪ መሆን ሳይሆን ፥ መመሳጠር ፥ ማሴር እና ወያኔን ቁስሉን መርገጥ ምን እንደሆነ የምናውቅ ልጆች ስለሆንን ፥ ያለ ቢሮ ፥ ያለ ማህተም ፥ ያለ ስብሰባ ፥ ያለ ጉራ፥ ያለ ያዙኝ ልቀቁኝ እናሸንፋለን ! አማራ ነና!

እርግጥ መሰብሰብ ያቃተን እንስመስላለን ። ግን ተበታትነንም አንድ ነን ! ነገን ማየት የማይችል ንጉስ ነገን ማየት ከሚችል እስረኛ አይሻልም ! የአማራ ህዝብ ነገን በባዶ ለመድረስ ፥ ቀፎ ድርጆቶን በመመስረት ጊዜያቸውን በሚያጠፉ ሳይሆን ፥ ነገን መነፀር በቻሉ ፥ ዛሬን በሚዋደቁ ቆራጥ ልጆች የተሰራ ቤት ነው ። ይህንን መንፈስ እንዴት አድርገህ ልትሰርቀው ትችላለህ። ግብዝ ካልሆንህ በቀር ልታስበውም አይገባህም ነበር ! ድንበራችንን ማስከበር የኛ ግዴታ ነው ! ማንም ይጩኽ ይንጫጫ ፥ በአማራ ህልውና ላይ አልደራደረም ! ከማንም ጋ ስለምንም ምክንያት ሲባል!

አማራ ተነስ!
ኄኖክ የሺጥላ

Share Button

ላይ ላዩን ሲታይ የአማራ ትግል ባለቤት የሌለው ይመስላል – ኄኖክ የሺጥላ