ግብፅና እኛ ( አብርሃ ደስታ )

ግብፅ ኢትዮጵያውያንን ደግፋ ፀረ የኢህአዴግ መንግሥት እንዲነሳ መቀስቀስ ከቻለች ኢህአዴግ ከግብፅ በላይ ለኢትዮጵያ ባዳ ነው ማለት ነው። ኢትዮጵያውያን ከኢህአዴግ በላይ ግብፅን ማመን ጀምረዋል ማለት ነው። ኢህአዴግ ኢትዮጵያውያንን በሚገድልበት ግዜ ህዝቡ በግብፅ ታግዞ ኢህአዴግን የሚቃወም ከሆነ ችግሩ የተቃዋሚው ህዝብ አይደለም። የግብፅም አይደለም። የኢህአዴግ መንግስት ችግር ነው። የኢትዮጵያ ህዝብ መደገፍ የነበረበት በባዕድ ሀገር ግብፅ ሳይሆን በራሱ በኢትዮጵያ መንግስት ነው። መንግሥት ህዝቡን ካልደገፈ፡ በአግባቡ ካላስተዳደረ በመንግሥትና በህዝብ መካከል ክፍተት ይኖራል። ክፍተቱን ተጠቅሞ ጠላት ይገባል። የዚህ ችግር ተጠያቂ ማነው? መንግስት ነው፤ የኢህአዴግ መንግሥት። ክፍተት መፍጠር አልነበረበትም። ኢህአዴግ በኢትዮጵያውያን ዘንድ የግብፅን ያህል እንኳ ተአማኒነት እስኪያጣ ድረስ ህዝብን መበደል አልነበረበትም፤ በግብፅ በሚታገዙ ኢትዮጵያውያን በኃይል እስኪባረር ድረስ በስልጣን መቆየት የለበትም። ኢህአዴግ እንደሚለው ህዝባዊ ተቃውሞው የግብፅ እጅ ካለበት ኢህአዴግ በግብፅ በመበለጡ ማፈር አለበት። ከግብፅ በላይ ጠላቱ ላደረገው ህዝብ ለማስተዳደርም የሞራል ብቃት ያንሰዋል።

እንደኔ ግን ህዝባዊ ተቃውሞው የግብፅ እጅ አለበት ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ተቃውሞው የህዝብ ነው። ህዝብ እንደ ህዝብ ደግሞ የሌላ ሀገር ድጋፍ ሊቀበል አይችልም። ሌላ ሀገር ሊሰጠው የሚችል ድጋፍ ቁሳዊ ወይ ሞራላዊ ነው። መንስኤ ለሌለው ነገር የሞራል ድጋፍ አይሰጥም። የሞራል ድጋፍ ዓመፅን ሊቀሰቅስ አይችልም፤ የተቀሰቀሰውን ዓመፅ ሊያቀጣጥል ግን ይችል ይሆናል። ቁሳዊ ድጋፍም የዓመፅ መንስኤ ሊሆን አይችልም። ሰው ለቁስ አካል መስዋእት አይሆንም። መስዋዕትነት ለነፃነት የሚከፈል ውድ ዋጋ ነው። እናም ህዝብ መስዋዕትነት እየከፈለ ያለው ለነፃነቱ ሲል እንጂ ከግብፅ ቁሳዊ ድጋፍ ስላገኘ ሊሆን አይችልም።

የፖለቲካ ቡድኖች ወይ ልሂቃን ግን የውጭ ሀገር ድጋፍ ሊቀበሉ ይችላሉ፤ እንደ ግብ ሳይሆን እንደ ታክቲክ። በትጥቅ ትግል የሚያምኑ የፖለቲካ ቡድኖች ኢህአዴግን አሸንፈው የስልጣን ወይ የዴሞክራሲ ዓላማቸውን እውን ለማድረግ የውጭ ሀገራት እርዳታ ሊጠይቁ ይችላሉ፤ ግብፅም ለራሷ ብሄራዊ ጥቅም ስትል በኢትዮጵያ ጉዳይ ሳትጠራ አቤት እንደምትል ሳይታለም የተፈታ ነው። አሁን ዋናው ጉዳይ ግብፅ መደገፏ ወይ አለመደገፏ አይደለም፤ ታጣቂ ቡድኖች የግብፅን ድጋፍ መቀበላቸው ወይ አለመቀበላቸውም አይደለም። ግብፅ ድጋፍ ትሰጣለች፡ ታጣቂ ቡድኖችም ድጋፉን ሊቀበሉ ይችላሉ። አሁን፡ ታጣቂ ቡድኖቹ የግብፅን ድጋፍን የሚቀበሉ ኢህአዴግን ከስልጣን አባረው የኢትዮጵያውያንን የዴሞክራሲ ፍላጎት ለማርካትና የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ነው? ወይስ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈው በመስጠት የግብፅን ብሄራዊ ጥቅም ለማስከበር ነው? ታጣቂዎቹ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያንን ክብርና ጥቅም ያስከብራሉ ወይ? ነው መጠየቅ ያለብን። (ህወሐትም ኮ ጫካ እያለ ከግብፅም ከሶማሊያም ከሌላም ድጋፍ ያገኝ ነበር። ዋናው ነጥብ ግን እሱ አይደለም፤ ድጋፍ አግኝቶ ስልጣን ያዘና ህዝብና ሀገርን ጠቀመ ወይ? ነው)።

ባጭሩ መጠየቅ ያለብን የችግሩ (የህዝባዊ ተቃውሞው) መንስኤ ምንድነው? ነው። በደል ነው። ማን የፈጠረው በደል? የኢህአዴግ መንግሥት። ለህዝባዊ ዓመፁ መነሻ የሆነውን በደልና ጭቆና እንዲሁም የነፃነት ጥያቄ በኢህአዴግ መንግስት የተፈጠረ ባይሆን እንኳ ኢህአዴግ ችግሩን መፍታት፡ ጥያቄውን መመለስ አልቻለም ማለት ነው። በዚህ ምክንያት የዓመፁ መንስኤ ኢህአዴግ ራሱ ነው ማለት ነው። የህዝብን የነፃነት ጥያቄ መመለስ የማይችል ድርጅት ለመንግሥትነት አይመጥንም።

ስለዚህ ለተፈጠረው ችግር በራስ ሐላፊነት ወስዶ ስልጣንን ከማስረከብ ይልቅ ግብፅንና አንዳንድ ተቃዋሚ ሐይሎችን ተጠያቂ ማድረግ ራስን ማታለል ነው። በመንግሥትና በህዝብ መካከል ክፍተት ባይፈጠር ተቃዋሚዎችም ግብፅም እንዴት መግብያ ያገኙ ነበር? ኢህአዴግ የመንግሥትነት ሐላፊነቱ በአግባቡ ቢወጣ ኖሮ እንዴት ክፍተት ይፈጠር ነበር?

የችግሩ መንስኤ ኢህአዴግ ነው። ስለዚህ የችግሩ መፍትሔ ኢህአዴግ ሊሆን አይችልም።

It is so!!!

Source Article from http://www.mereja.com/amharic/517673

ግብፅና እኛ ( አብርሃ ደስታ )