“በስህተት ነው ፍ/ቤት ያቀረብንህ” – ወሰንሰገድ ገብረኪዳን

#MALAAN_JIRA
“በስህተት ነው ፍ/ቤት ያቀረብንህ” – ወሰንሰገድ ገብረኪዳን
============
“MALAAN JIRA” “ማለን ጅራ” የሀጫሉ ሁንዴሳ Hacaaluu Hundessaa ዘፈን ነው፡፡ ባለፈው ዓመት ነው የተለቀቀው፡፡ ኦሮምኛ አልችልም፡፡ ለምን እንደሆን እንጃ የሀጫሉን “ማለን ጅራ” ግን እወደዋለሁ፡፡ በእኔ ዕይታ የዜማው ፍሰት፣ የክሊፑ ቅንብር … ወዘተ የተዋጣለት ነው፡፡ መልዕክቱ ባይገባኝም ዘፈኑ የሆነ የሚመስጥ፣ የሚወዘውዝ ነገር አለው፡፡ ይሁን እንጂ የዘፈኑን ርዕሱስ እንኳ አላውቅም፡፡ በኋላ ግን ወደ ኢንተርኔት ጎራ ብዬ ርዕሱን አየሁ፡፡ እስረኛውን ጠይቄ ስመለስ ዜማውን ብቻ እያንጎራጎርኩ ነበር፡፡ እናም የዘፈኑን መልዕክት የመረዳት ጉጉት አደረብኝ፡፡ ጥቂት ካሰብኩ በኋላ ከፌስቡክ ጓደኞቼ አንዱን በውስጥ መስመር ጥያቄ ሰደድኩለት፡፡
.
“ከዘፈኑ መሃል አንድ አራት መስመር ተርጉመህ ንገረኝ?” አልኩት፡፡
“ዘፈኑ ቃል በቃል ሲተረጎም ደረቅ ነው ሚሆነው፤ ብዙም አይጥምም” አለና ጥቂት ስንኞችን ተርጉሞ ላከልኝ፡፡
.
“Gasraa abbichu turii
አብቹ ጋራ ቆዪኝ
Galaan Finfinnee marsee
ገላን ፊንፊኔን ከቦ ነው ያለው
Silaa akka jallalaa wal-irraa fadaannu jaratu nu fagaeesse
እንደፍቅራችን መራራቅ የለብንም ነበር ሰዎች ናቸው ያራራቁን
Diiganii gaara sanaa diigamuu hin mallee,
ያ ሊናድ የማይችለው ተራራ አፍርሰው አፈራርሰው
Baasani nu addaan baanee
ለይተው እኛን ለያዩን
nuti addaan bahu hin mallee.
ልንለያይ የማይገባንን
መፍረስ የሌለበት ያንን ጋራ (ተራራ) አፈረሱት ተለያየን ለያዩን እንጂ እኛ መራራቅ አልነበረብንም
Soreetti haadha sooree
ሃብታሟ የሃብታሙ እናት
irbaan irra buusa qaba,
እራት ጭማሪ አለው
seeqanii sesseeqanii
ጋፍተው ገፋፍተው
kan addaan nu baasan jara….
ሰዎቹ ናቸው የለያዩን
.

የዘፈኑን ትርጉም በከፊል በተረዳሁ ጊዜ ከሳምንት በፊት የሴት አያቴ ወንድም መጥቶ ያወጋነው ታወሰኝ፡፡ እህቱን (ሴት አያቴን) ሊጠይቅ መጥቶ ነበር በዚያው ወደእኛ ቤት ጎራ ያለው፡፡ ከፍቼ /ኮማንዶ/ ትንሽ ወጣ ብሎ “ቦሴ” የሚባል መንደር ነው የሚኖረው፡፡ ቆፍጣና ገበሬ ነው፡፡ እስከዚህ ዕድሜዬ ድረስ አንድ ጊዜ ብቻ ነው ቦሴ ሄጄ የጠየቅኩት፡፡ እሱንም የልጁን ሠርግ ተጠርቼ መሰለኝ፡፡ እሱ ግን (የሴት አያቴን ወንድም አንተ የምለው እሱ ራሱ “አንተ” በለኝ ብሎ ነው) በየዓመቱ ወይ በየሁለት ዓመቱ አዲስአበባ መጥቶ ይጠይቀናል፡፡ በመጣ ቁጥር “እናንተማ ዘመድ አትጠይቁም፤ ተለያይተን መቅረታችን ነው” እያለ ይወቅሰናል፡፡ (መቼም የሀጫሉን ዘፈን ሰምቶ አይመስለኝም ሁሌም “ተለያይተን ልንቀር” የሚለው)
የሆነ ሆኖ እንዳየሁት “አረጀህ እኮ” አልኩት፡፡
“ምን እኔን አረጀህ ትለኛለህ? አንተ ራሱ ጨርጭሰህ የለ እንዴ” አለኝ፡፡ ሳቅኩኝ፡፡ እውነቱን ሳይሆን አይቀርም፡፡ እሱ አሁንም ጠንካራ ነው፡፡
“እንደዚህ ያገረጀፈህ የከተማ ኑሮ አስንፎህ ስራ ስለማትሰራ ነው፤ እኔ ጋ ብትመጣ እንደገና ልጅ ትሆናለህ”
“እዛ መጥቼ ምን እሰራለሁ?”
“መቼም እርሻ ማረስ አትችልም፡፡ ሁለት ላም እሰጥሃለሁ፤ ከብት ታረባለህ” አለኝ፡፡
ገበሬ ስሆን ታየኝና ሳቅኩ፡፡
.
እና ….. ይህንን ትውስታዬን እያመነዥግኩ “አሁን ፍቼ/ቦሴ አያቶቼ መንደር ብሄድ ኮማንድ ፖስቱ የሃጫሉን ዘፈን ሰምተህ ነው ሊለኝ ነው?” ብዬ ራሴን ጠየቅኩ፡፡ እዚህ አገር መቼም እፍረት የሚባል የለ፤ እንደዛ ይሉ ይሆናል፡፡
.
ምክንያቱም መዝናኛ ቤት (መጠጥ ቤት) ይህንኑ የሀጫሉን ዘፈን እንዲከፈት ጠይቀሃል ተብሎ ጋዜጠኛ ኢዩኤል ፍሰሃ እስር ቤት ተወርውሯል፡፡ ከወራት በፊት፡፡ ኢዩኤል ከእስር የተፈታ መስሎኝ ነበር፡፡ አንዳንዴ እንዲህ ይሆናል፡፡ የተፈታ የመሰለኝ ነገሩን (የታሰረበትን ምክንያት) አቅልዬው ይሆናል፡፡ እነ አናንያ እና ኤልያስ ናቸው አሁንም በእስር ላይ መሆኑን ነግረው ያስታወሱኝ፡፡ ስለዚህ ልጠይቀው ችሎት ተብሎ ወደሚታወቀው አካባቢ የሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ሄድኩ፡፡
.
ወደፖሊስ ጣቢያው የሚያዘልቀውን ኮረኮንች ይዤ ትንሽ እንደተጓዝኩ ያየሁት ነገር አጠራጥሮኝ ቆም አልኩ፡፡ የተሳሳትኩ መሰለኝ፡፡ በሩ አናት ላይ ትልቁ “የአራዳ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ክሊኒክ” የሚል ፅሁፍ ይታያል፡፡ እንደመጠራጠር አልኩኝና በአጠገቤ የሚያልፉ ሰዎችን “እስረኞች ያሉት እዚህ ነው አይደል?” ስል ጠየቅኩ፡፡ “አዎ” አሉና አረጋጡልኝ፡፡ “ክሊኒክ” የሚለውን እንደገና ፈገግ አልኩ፡፡ ወደው አይስቁ አለ ያገሬ ሰው፡፡
.
ገባሁ፡፡ ኢዩኤልን አስጠራሁት፡፡ መጣ፡፡ የተደነቀ ይመስላል፡፡ በእጁ መፅሐፍ ይዟል፡፡ ተጨባበጥን፡፡
“እዚህ መፅሐፍ ይገባል እንዴ?”
“አዎ፤ ይገባል”
“እኔ ምልህ፤ ከታሰርክ ስንት ጊዜ ሆነህ”
“አራት ወር ከ4 ቀን….ዛሬ 124 ቀኔ እዚህ ከተጣልኩ”
“ፍ/ቤት ቀርበህ…ዋስትና እንደተፈቀደልህ ያነበብኩ መስሎኝ ነበር”
“አዎ እንደታሰርኩ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍ/ቤት ቀርቤ የሁለት ሺህ ብር ዋስትና እንዳቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶ ነበር”
“እና…?”
” ዋስትናውንም አስይዤ መፈቻ መጥቶ ነበር፡፡ እዚህ መፈቻው ላይ አንፈርምም ብለው ይኸው እስካሁን አለሁ”
“ለምን? ለምን እንዳለቀቁህ አልጠየቅክም”
“መጠየቅማ ጠይቄአለሁ፡፡ መጀመሪያውኑ ፍ/ቤት መቀረብ አልነበረብህም፡፡ በስህተት ነው ፍ/ቤት የቀረብከው …አሉኝ”
“ምን ማለት ነው?”
“እኔም ምን ማለት እንደሆነ አልገባኝም….” አለኝ ግራ በተጋባ ስሜት፡፡
.
እነሆ ጥቂት ደቂቃ እንዲህና እንዲያ አውግተን ተለያየን፡፡ እናም ተመለስኩ፡፡ “ማለን ጅራ”ን እያንጎራጎርኩ፡፡ አሁን ማለት የምችለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እሱም ሰሚ ከተገኘ!
.
#ኢዩኤል_ፍሰሃ_ዳምጤን_ፍቱት!

“በስህተት ነው ፍ/ቤት ያቀረብንህ” – ወሰንሰገድ ገብረኪዳን