የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች! – አቻምየለህ ታምሩ

አቻምየለህ ታምሩ

የኢሳያስ አፈወርቂ የቅርብ አማካሪ፣ የአስመራ ዩኒቨርሲቲ ምክትል ፕሬዝደንትና የሻዕብያ ፋኖ የነበረው ኤርትራዊው ፕሮፌሰር አስመሮም ለገሰ የOromo Studies Association (OSA) ባዘጋጀው ጉባዔ ላይ ቀርቦ «የኦሮሞ ሪፑብሊክ የበለጠ ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የጋዳ ስርዓት ማስተካከል አለበት» ያላቸውን አንድ ሶስት ምክሮች ለታዳሚው ለግሷል። ጉድ በል ጎንደር ነው። ኤርትራ ዲሞክራሲ ጠግባ «በጎረቤት ሀገር» ዲሞክራሲ እንዴት መስፋት እንዳለበት ተሞክሮ ለማካፈልና ለማዋስ ስትበቃ እንደማየት ምን አስቂኝ ነገር አለ? ያገራችን ሰው የአስመሮም ለገሰ አይነቱን ልኩን የማያውቅ ነውረኛ «የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች» ይለዋል።

ሻዕብያው አስመሮም ለገሰ አንድን አገር ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚተርፍ ምክረ ሀሳብ ካለው «ለሰላሳ አመታት ያህል ዲሞክራሲና ነጻነት ለማምጣት ታገልንላት» የሚሏት አገራቸው ድቅድቅ ጨላማ ውስጥ ወድቃና በፕሮፌሰር ተስፋጽዮን መድሃኔ አገላለጽ «ኤርትራ ሞተች» እየተባለ ለመሰሪ አላማው በማያገባው ጥልቅ ብሎ የሚዘረጋውን ምላሱን «ሞታለች» እየተባለች ላለው የራሱ አገር ኤርትራ «ትግል ለሀገር ትንሳኤ» አካሂዶ ለምን መጀመሪያ ዲሞክራሲያዊት አገር አያደርግበትም? አስመሮም ለገሰ የራሱ እያረረበት የሰው የሚያማስለው «የኦሮምያ ሪፑብሊክ» የሚላትን ምክር የሚለግሳት «አገር» ከኤርትራ አስበልጦ ስለሚወድ ነው የሚል የዋህ መቼም ይኖራል ብዬ አልገምትም።

መላው አለም ማዕቀብ አድርጎበት ጣዕረ ሞት ላይ ካለውና ከዛሬ ነገ የአለም ጦር ፍርድ ቤት ይቀረባል እየተባለ ከሚባንነው ጉድ ከኢሳያስ እቅፍና ከሻዕብያ ጓዳ «የኦሮሞ ሪፑብሊክን» የበለጠ ዲሞክራሲያዊ ለማድረግ የሚያስችል የተውሶ ምክረ ሀሳብ እንዴት ሊገኝ እንደሚችል የገባው ካለ ቢያስረዳኝ ወሮታውን እከፍላለሁ።

የተማሩ ሰዎች ጉባኤ አላማው የተሻለ አድማስ ለመፍጠርና ምርጥ ተሞክሮ መፈለጊያ መነጸር ለማጥለቅ ይመስለኝ ነበር። ከሻዕብያ ጓዳ ዲሞክራሲን ለማስፋት በሚሰጥ ምክረ ሀሳብ ዙሪያ ለመምከር ከሆነ ግን ምክረ ሀሳቡም የተማሩ የተባሉትም ጥንቅር ብለው ቢቀሩና መሀይም እንዳሻው ቢገድል ይሻላል።

የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች! – አቻምየለህ ታምሩ