በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን የውጭ ኃይሎች ሴራ እንዴት ለመቋቋም እንችላለን? – አክሎግ ቢራራ (ዶር)

–ካለፈው ታሪካችን በመማር–

ክፍል ሶስት

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

አክሎግ ቢራራ (ዶር)

ያለፉት አምሳ ዓመታት የፖለቲካ ታሪካችን የሚያሳየን ግድፈት ወይንም ድክመት (Failure) ካለፈው ተምረን የወደፊቱን ለማሻሻል ሞክረን አናውቅም። የአቋም ግትርነት ከባህርያችን ጋር ተቆራኝቷል። በክፍል አንድና ሁለት የቀረቡትን ተግዳሮቶች ሰብሮ ለመውጣትና  አቅጣጫዎችን ስኬታማ ለማድረግ የጋራ አገር አለን ማለትን፤ የጋራ ዓላማና እምነት አለን ማለትን፤ የጋራ ብሄራዊ ዓላማ አለን ማለትን ይጠይቃል። ለጋራ የሃገር ደህንነትና ቀጣይነት፤ ለጋራ ጥቅምና ዘመናዊነት፤ ለጋራ ፍትሃዊና ዘላቂ እድገት ተባብረን ለመስራት የምንወስንበት ወቅት አሁን ነው። ኢትዮጵያ ከፈረሰችና የእርስ በርስ ግጭት ከተነሳ በኋላ አይደለም። ጊዜ የለንም። አምስትና አስር ዓመታት እንጠብቅ፤ እንቆይ ካልን ኢትዮጵያን እናጣታለን!!

ኢትዮጵያን ለማዳን የምንችለው እኛው ብቻ ነን። ኢትዮጵያ ብትፈራስ አዲስ ህይወት እናገኛለን የሚሉ ወገኖች ተሳስተዋል። ገና ያላዩት ነገር ይናፍቃል እንጅ ይህች አገር ከፈረሰች ከሶማልያና ከሶሪያ የየባሰ ሁኔታ ይከሰታል። በአዲስ አበባ ሆነ በሌላ ከተማ የምናየው ሰማይ ጠቀስ ህንጻ፤ ተወዳዳሪ የሌለው ቪላ፤ መሰረተ ልማት ወዘተርፈ ይወድማል።

ኢትዮጵያን እንድትፈርስ ያደረግናት ራሳችን ነን። ለክፉም ለደጉም ልምዱ አለን። የሚጠይቀው ከቡድን ወይንም ከፓርቲ ወይንም ከጎሳ ወይንም ከኃይማኖት ጥቅም በላይ ሃገርንና መላውን ሕዝቧን ማስቀደምን! ከመጠላለፍና እርስ በርስ ከመነታረክ በፊት መደማመጥንና መቻቻልን! አንዱ ከሌላው ለመማር ፈቃደኛነትን! የእኔ አጀንዳ ይቅደም ከማለት በፊት እየተናበቡ በጋራ ብሄራዊ ዓላማ ላይ የተመሰረተ የጋራ ራእይንና ተልእኮን ማመቻቸትን! ይሆናል። ይኼን ለማድረግ ያልቻልነው እኛው ነን። ፈረንጆች አስገድደውን አይደለም።

ላለፈው ጥፋት ወይንም ድክመት ቂም በቀለኛነትን ማስተጋባት አያዋጣም። ያለፈው አልፏል። የአገራችን ሁኔታ የሚጠይቀው ጥፋቶችን አምኖና ተቀብሎ የመተማመንን ባህልን ማጠናከርን ነው። የድብቅ አጀንዳን ልማድ ከማድረግ ይልቅ ግልጽነትን፤ ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን የባህሎቻችን አካል ማድረግ ወዘተ ለዲሞክራሳዊ ስርዓት ግንባታ ወሳኝ ናቸው።

የአስተሳሰብ ለውጥ ወሳኝነት (The imperative of a paradigm shift)

ከተማሪው እንቅስቃሴ (1960s and early 1970s) ጀምሮ እስካሁን (2017) የተገነዘብኩት አንዱ ትምህርት እኛ “ምሁራንና ልሂቃን ነን” ብለን ራሳችን የምንሰይም ግለሰቦች የሃሳብ መሪዎችና ቡድኖች ወደኋላ ዘወር ብለን በማሰብ “ምናልባት እኔኮ ተሳስቸ ይሆናል፤ የተናገርኩት ሌላውን ሰው አስቀይሞት ይሆናል፤ ለሃገራችን አደጋዎች ፈጣሪና አስተጋቢ ይሆናል” ለማለት የማንደፍር መሆናችንን ነው። የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል ስል “ምናልባት እኔ ተሳስቸ ይሆናል፤ እስኪ ከመናገር ማዳመጥንና ራሴን መመራመርን ላስቀድም” የሚለውንም እናስብበት ማለቴ ነው። ሌላውን ማማት፤ ሌላውን ማውገዝ መቆም አለበት!! መጀመሪያ የራሳችንን ስህተት እንቀበል!!

መኖር ብዙ ነገሮችን ያሳያል። የሌሎች አገሮችን ልምድ ማየት አስተሳሰብን ያሰፋል። እኛ ኢትዮጵያዊያን ከዚህ በፊት የተጓዝንባቸውን የፖለቲካ መንገድ ግድፈቶች በጽሞና ብናጤናቸው ከራሳችን የፖለቲካ ታሪክ ብዙ ለመማር እንችል ነበር። ችግሩ ስህተቶችን መስራቱ አይደለም። ችግሩ ከስህተቶች ለመማር አለመቻላችን ነው። ከስህተት አለመማር በራሱ አስለች ነው። በተጨማሪ፤ የእኔ ትውል ለአሁኑና ለተከታታይ ትውልድ መንፈስን፤ ህይወትን፤ አገርንና ህብረተሰብን የሚለውጡ ወይንም የሚያድሱ ሃሳቦችን ሊሸምት የሚያስችል ትምሕርት እንዲያገኝ አላስቻልነውም። የአሁኑና ተከታታይ ትውልድ ከብሄር ጥላቻ፤ ከመናናቅ፤ ከምቀኝነት፤ ከቂም በቀልነት ምን ለማስተማር ይቻላል? አይቻልም።

ያለፈውን በግድፈት፤ በቂም በቀልነት፤ በጥላቻ ወዘተርፈ የተበከለ የፖለቲካ መንገድ ለአንድ ደቂቃ ዞር ብለን ብናስተውለውና ከአሁን በኋላ ከአብሮ መስራት ውጭ ሌላ አማራጭ የለም! አገርንና ሕዝብን ከማስቀደም ሌላ አማራጭ የለም! ከመቻቻልና ለሌላው ግለሰብ፤ እንደ ኢትዮጵያዊነቱና እንደ ሰብእነቱ ከማሰብ፤ “ነግ በእኔ” ከማለት (Empathy) የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ የሚያስችል መንገድ የለም! ብለን አብረንና ተባብረን ለመስራት ብንችል ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ ከፍተኛ አስተዋፆ ለማድረግ እንችላለን። ልዩነት ጤናማ ነው። ልዩነት እንዳለ ሆኖ፤ አንዱ ሌላውን ማዳመጥ፤ አንዱ ከሌላው ለመማር ፈቃደኛ ቢሆን ለኢትዮጵያና ለመላው ሕዝቧ አዲስ ምእራፍ ይከፍታል። የማያዋጣው ጊዜ ያለፈበት መንገድ “የእኔ አስተሳሰብ፤ የእኔ ድርጅት” ብቻ (My Way or the Highway) የሚለው ጊዜ ያለፈበት ጎዳና ነው።

በተደጋጋሚ ከባለሞያዎች የምንሰማው እንዲህ የሚል ነው። “አንድ ግለሰብ ለመመራት ካልቻለና ፈቃደኛ ካልሆነ፤ ለመምራት አይችልም፤ የሞራል ብቃት የለውም። አንድ ግለሰብ ከሌላው ለመማር ካልቻለ ለማስተማር አይችልም፤ ራሱን ለመለወጥ አይችልም።” ራሳችን ለማሻሻል ስንል፤ ለትምህርት ያለን ትጉህነትና ታታሪነት በጣም አስደናቂ ሆኖ ሳለ ከእርስ በርሳችን ለመማር፤ ለሃገርና ለሕዝብ ጥቅም ስንል ለመመራትና ሕብረተሰቡን ለማገልገል ያለን ፍላጎት በጣም ዝቅተኛ ነው። ይህ ከቀጠለ እውነተኛ ዲሞክራሲን ለመመስረት አንችልም። ካልቻልን ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፤ ከፈረሰች ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ይጎዳሉ። ዲሞክራሲ የቡድን፤ የማህበረሰብና የህብረተሰብ ስፖርት እንጅ የግለሰብ ስፖርት አይደለም። የአስተሳሰብ ለውጥ፤ መተባበርን፤ መተሳሰብን፤ መደማመጥን፤ መደጋገፍን ወዘተርፈ ይጠይቃል።

በመተባበር፤ በመደጋገፍና በጋራ ጥቅም የተመሰረተ የፖለቲካና የእድገት ባህል ስር እንዲሰድ ከፈለግን መጀመሪያ የአስተሳሰብ ለውጥ በማድረግ የኢትዮጵያን ዘላቂነትና የስብጥር ሕዝቧን አንድነት የታሪክ ሂደት ተቀብለን፤ የኢትዮጵያንና የመላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ዘላቂ ጥቅም እናስቀድም ለሚል መርሆ የማያወላውል ትኩረትና ቅድመት መስጠት ግዴታችን ነው።

ኢትዮጵያን እኛ ካላቀደምን ማን ሊያስቀድምልን ነው? የእያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ መብት ካላስቀደምን ማን ሊያስቀድምልን ይችላል? አንዱ ወገን በሌላው ላይ የሚደረገውን ሃሜት፤ የጥላቻ መርዝና ሕዝብን መከፋፈል ስንሰማና ስናይ ለምን በድፍረት ይኼ ትክክል አይደለም ለማለት አንችልም? ብሄራዊ ጥቅም በመሸነጋገል ስኬታማ አይሆንም።

ብሄራዊና ሕዝባዊ ጥቅሞች ተቀዳሚ ይሁኑ ስል የሁሉም ብሄርና ኃይማኖት አባላት መብትና ጥቅም ይከበሩ ማለቴ ነው። የኢትዮጵያን ብሄራዊ ጥቅም፤ የኢትዮጵያን ቀጣይነትና ሉዐላዊነት እናስቀድም የሚለው መርህ የሁሉም ብሄሮች ግዴታ ነው። ይኼን የጋራ ብሄራዊ ዓላማ የሚጻረሩትን ግለሰቦችና ቡድኖቾ ደፍረን ለመተቸትና ለመናገር መቻል አለብን።

እኛ አገራችን ለቀን ወደ ሌላ አገር (አሜሪካ፤ ካናዳ፤ አውስትራሊያ፤ ጀርመኒ ወዘተ) ስንሰደድ የተሰደድንበትን አገር የሕዝብ ስርጭት፤ ባህል፤ ኃይማኖት፤ ፖለቲካ ወዘተ ያለ ማመንታት እንቀበላለን። ሰዓትና አለቃ እናከብራለን። ለብዙዎቻችን የጋራ የሆነችውን እናት አገር ታሪክና ሌላ ለመቀበል፤ አገር ወዳድ መሪዎችን ለማፍራትና ለመንከባከብ በጣም ያስቸግረናል። በአገራችን ግፍና በደል ይፈጸማል ካልን በኋላ በካናዳ፤ በአሜሪካ፤ በአውሮፓና በሌሎች አገሮች አቤቱታ የምናቀርበው በተናጠል፤ በጎሳ፤ በኃይማኖትና በሌሎች መለያዎች ነው። አማራው ለአማራው!! ትግራዩ ለትግራዩ!! ኦሮሞው ለኦሮምው!! አኟኩ ለራሱ ብሄር!! ሶማሌው ለራሱ ወዘተርፈ ይቁም የሚለው የማንነት መርህና አቋም ኢትዮጵያዊነትን አድክሞታል። ስለደከመም የምንጋራው እሴት የለም የሚለው ባህል ስር እንዲሰድ ተደርጓል።

የምንጋራት አገር አለችን ወይንስ የለችንም?

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ኢትዮጵያን፤ የተፈጥሮ ኃብቷን፤ ባጀቷን በበላይነት ተቆጣጥረው በማንም አገር ታይቶ የማይታወቅ የግል፤ የቤተሰብና የፓርቲ ኃብት ያካበቱት ህወሓቶችና ተባባሪዎቻቸው ከዚህች ኃብትና ክብር ካስገኘችላቸው አገር ጋር ምን ተቃርኖ እንዳላቸው ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚገልጹበት አዲስ የዘመን መለወጫ ዓመት በዓል እንዲከበር ህወሓት/ኢህአዴግ ሰብኳል፤ ሕዝቡ በዓሉን የሚያከብርበትን ሁኔታ ግን አላመቻቸም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ገዢዎች ከሕዝቡ ጋር ተጣልተዋል የሚሉ ብዙ ናቸው። ከሕዝቡ ጋር ተቃርኖ ከሌላቸውና የኢትዮጵያ ሕዝብ ተቻችሎ እንዲኖርና ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከድህነት ነጻ ወጥተው ራሳቸውን እንዲችሉ ፍላጎት ካለ፤ አገሪቱን በክልል ለያይተው፤ አንቀጽ 39 መመሪያቸው አድርገው ወዘተ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ የጫኑትን ሕገ መንግሥት የሚቀይሩበት፤ ቢያንስ የሚያሻሽሉበት ወቅት አሁን ነው። ጠባብ ብሄርተኝነት የማያዋጣና አገርንና ህብረተሰብን ከፋፋይ መሆኑን ተቀብለው ኢትዮጵያዊነት የሚያኮራ የዜግነት መለያችን መሆኑን ይፋ የሚያደርጉበት ወቅት ዛሬ ነው።

እነዚህ አዲስ ባለ ኃብቶችና ባለሥልጣናት የኢትዮጵያና የመላው 105 ሚሊየን ሕዝቧ ባለ ውለታ ናቸው። ከድህነት ስቃይ ነጻ ያወጧቸው ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ ናቸው። ለሁለቱም ኃላፊነት አለባቸው። የመጀመሪያው ሃላፊነት የኢትዮጵያን ታሪክ ተቀብሎ ግዛታዊ አንድነቷን፤ ዳር ድንበሯን፤ ቀጣይነቷን፤ ብሄራዊ ጥቅሟን፤ ሉዐላዊነቷንና ክብሯን በማያሻማ ደረጃ ማክበርና ማስከበር ነው።

ጠባብ ብሄርተኝነት፤ ጎጠኝነት፤ አድሏዊነት ወዘተ ከቀጠለ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ወክሎ የሚናገር ማን አለ? የምንሰራውና የምንናገረው ሁሉ ኢትዮጱያን የሚያጠፋ ከሆነ የጋራ አገር አለን ለማለት የምንችልበት ሁኔታ የት ላይ ነው ያለው? ለዚህች ኢትዮጵያ ለምትባል አገር ማን አቤቱታ ያቅርብ? ወደ ተባበሩት መንግሥታት ብንሄድ ይስቁብናል!!

በዚህ ሁኔታ ወደፊት የሚከሰተውን ሳስብ እንቅልፍ አይዘኝም። የወደፊቱን (የዛሬ አምሳና መቶ ዓመታት) ስናጤን ዛሬ የምንኖርበት ዓለምና የወደፊቱ ዓለም በጣም የተለያዩ እንደሚሆኑ ማሰብ ግዴታችን ነው። ይህን የማይታወቅ ዓለም የልጅ ልጆቻችን እንዲዘጋጁበት ከፈለግን ጠባብ ብሄርተኝነትን ማስወገድ፤ አብሮና ተደጋግፎ መኖርን ማስቀደም ግዴታችን ነው። የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። የሕዝብ ቁጥር መጨመር በተናጠል ችግር አያመጣም። ችግር የሚፈጥረው መቻቻልና መግባባት አለመኖሩ ነው። ዛሬ የፖለቲካ በሽታችን ሁሉም “እኔ መሳፍንት ነኝ፤ ግዛቴና የተፈጥሮ ኃብቴ ይከበር ማለቱ ነው።” ከወገኑ ጋር ተቻችሎ ለመኖር የማይችል ሕዝብ የሚኖረው እጣ ሶማሊያን፤ ደቡብ ሱዳንን፤ አፍጋኒስታንን፤ ሶሪያን የሚመስል ነው። ኢትዮጵያዊያን በገፍ አገራቸውን የሚለቁበት ምክንያት ተስፋ ስለቆረጡ ነው። የወደፊቱን ዓለም “በአገራችን ሆነን ልንወጣው አንችልም” የሚል መልእክት እየላኩ ነው።

የወደፊቱን ዓለም የሚቆጣጠሩት ኃይሎች ለዲሞክራሲ፤ ለፍትህ፤ ለሕግ የበላይነት፤ ለእውነተኛ እኩልነት፤ ችግሮችን በመወያየትና በመግባባት ለመፍታት ለቆረጡ፤ ስግብግብነትን አስወግደው ያላቸውን የተፈጥሮና የገንዘብ አቅም ለጋርዮሽ ዓላማዎች ለማዋል የቆረጡ ሕብረተሰቦች ነው። ባለሞያዎች እንደሚሉት ወደፊት የሚከብሩትና አደጋዎችን የሚወጡት ዜጎች በማህበረሰባዊነት በጋራ ጥቅም የሚያምኑ ናቸው (Those with community and solidarity spirit). ከተሜነት እየተስፋፋ ሲሄድ በሕዝቦች መካከል ያለው ግንኙነት መቻቻልን፤ አብሮና ተካፍሎ መኖርን ይጠይቃል። በስግብግብነት የተበከለው የምእራብ ሊበራል ካፒታሊዝም ለዚህ ፍትሃዊ ለሆነ አዲስ ስርዓት የተዘጋጀ አለመሆኑን ሊቃውንት ሲተቹት ቆይተዋል። እነሱ ዓለምን የሚያሽረክሩት በየአገሩ እንሱን መሰል የጥቅም ሊሂቃንን (Social Elites) በመፍጠርና በመንከባከ  መሆኑን ባለሞያዎች ይጠቅሳሉ። እነዚህ ለራሳቸው ጥቅም የፈጠሯቸው ማፊያ የሚመስሉ ቡድኖች የፖለቲካ ስልጣን እየያዙ ሽብርተኛ የሆነ የመንግሥት ስርዓት (Terrorist State and Government) መስርተው ሌላውን በሽብርተኛነት የሚከሱበትና የሚያሰቃዩበት ዋና ምክንያት የውጭ ደጋፊ ስላላቸው ነው። ሁለቱም ኃይሎች ለሃገር ወዳዶችና ለማህበረሰባዊ ዲሞክራሲ (Social and Participatory Democracy ጠላት ናቸው። (Robert Gaylon Ross, The Men Who Really Run the World, H. Paul Jeffers, History’s Greatest Conspiracies.

በጀፈርስ (Jeffers) ጥናት መሰረት እንደምናየው አሜሪካኖች ታዳጊ አገሮችን ለራሳቸው ጥቅም አመች በሆነ ስልት ለመቆጣጠር የቻሉት በሚፈልጓቸው አገሮች የጥቅም ተባባሪዎችን በመፍጠር ነው። ይህ የሚደረገው በዘፈቀደ አይደለም። በብዙ ጥናት፤ ምርምርና ውይይት ነው። “International elites of politics, industry, commerce, diplomacy, leaders of the communications and news media, intellectuals; and the military” and global bodies such as the IMF, the World Bank, WTO, the World Court and numerous others are part of the humongous non-elected body of people and institutions that run the world” convene in secret and in public and manage our complex world in accordance with their own needs.  በተለይ፤ የአሜሪካኖች የበላይነት በዶሚኒካን ሪፐብሊክ፤ በኢራክ፤ በአፍጋኒስታን፤ በሻሁ መንግሥት በኢራን፤ በግብጽ፤ በደቡብ ኮሪያና በሌሎች አገሮች የሚካሄደው አገር ወዳድ መንግሥታትን በመገልበጥና ለአሜሪካኖች አመች በሆኑ ቡድኖች በመተካት ነው። የሃሳብ ተቋሞችና “የበጎ አድራጊዎች (Good Samaritans) ዋና ስራም ይኼው ነው። “The annual and exclusive retreat of America’s elites, the rich and powerful, including U.S. Presidents, cabinet officials, directors and officers of corporations, bankers, financiers, military contractors, leaders of the oil industry and nuclear power companies, and journalists” is not to make the world a better place for the billions of people who inhabit this planet. It is to preserve power, privilege and influence.

በዳቮስ (Davos) ሆነ በአሜሪካ በሚደረገው የግል ስብሰባ ኃይልና ኃብት ያላቸው ግለሰቦች ሲሰበሰቡና ሲመካከሩ የበለጠ ኃይለኛ፤ የበለጠ ኃብታም ይሆናሉ። በተባበሩት መንግሥታት ተቋማትም ያለው ሁኔታ የተለየ አይደለም። እኛ እርስ በርሳችን እየተባላን እነዚህ ኃይሎች ጥቅማቸውን ይስከብራሉ።

ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎችን ያለፈችና አሁንም በብዙ ፈተናዎች የተበከለች አገር ናት። ይኼን ሃተታ እንድጽፍ የተገደድኩበት አበይት ምክንያት ይህች ረዥም ታሪክ ያላት፤ ታላቅና ለሁሉም ዜጎቿ የሚበቃ የተፈጥሮ ኃብት ያላት አገር በራሷ ልጆች ስትጠቃ ማየቴ ነው። ፊት ለፊት የሚታገሉላትና ደፍረው ለታላቅነቷ፤ ለቀጣይነቷና ለሉዐላዊነቷ የቆሙላት እየቀነሱ፤ እንደ ህወሓት ፊት ለፊት አትራፊና ዘራፊ ሆነው ኃብት እያካበቱና ከጀርባ ሆነው ታላቋ ኢትዮጵያ “ትንሽ” አገር እንድትሆን ቀን ከሌት የሚሰሩት እየጨመሩ ሲሄዱ የቀድሞ አባቶቻችንና እናቶቻችን ምን “ሃጢያት” ሰርተው ይሆን? የሚል ጥያቄ አነሳለሁ። ለዚህ መልስ ለማግኘት ቀላል ስለሆነ የታሪክ መጻህፍቶችን አነባለሁ። ታሪካችን የሚያኮራ መሆኑን እንደ ገና አረጋግጨ ችግሩን የፈጠርነው “እኛው ነን” ወደሚለው የተለመደ ድምዳሜ አመራለሁ። ከዚያም መፍትሄውን ከእኛ ሌላ ማንም ሊሰጠን አይችልም እላለሁ።

ያለፈውና የአሁኑ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚነግረን ታሪክ የውጭ ኃያላን መንግሥታት፤ ድርጅቶችና ግለሰቦች አገር ቤት ካሉት ጋር በመመሳጠር ኢትዮጵያ ነጻ፤ የተከበረች፤ የተባበረችና ኃብታም አገር እንዳትሆን ብዙ ሴራዎችን አካሂደውባታል፤ አሁንም እያካሄዱባት ነው። ይህን የሚያደርጉት ተጠቃሚዎችን በመፍጠር፤ በየድርጅቱ በማስገባት፤ መሸሸጊዎች በማመቻቸት ወዘተ ነው። ይህን ግዙፍ ችግር ልንፈታው የምንችለው በአሁኑ የብሄር/ቋንቋ ፌደራሊዝም ስርዓት ሊሆን አይችልም። በመከፋፈልና በመበታተን ሊሆን አይችልም። ሕዝቡ የፖለቲካ ስልጣኑ ባለቤት እንዲሆን በማመቻቸት፤ የሃገራችን የተፈጥሮ ኃብት ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጥቅም እንዲውል ያልተቆጠበ ጥረት በማድረግ ብቻ ነው። ይህን ለማድረግ እውነተኛ ዲሞክራሲ አስፈላጊ ሆኗል።

ህወሓት/ኢህአዴግ ሰላምን፤ መቻቻልን፤ እርጋታን አይፈልግም። ያስጠቃኛል የሚል ግምትና እምነት አለው። የኢትዮጵያን ቀጣይነትና ሉዐላዊነት ያለማወላወል አይቀበልም። በኦሮሞና በሶማሌ ብሄር ኢትዮጵያውያን መካከል የእርስ በርስ ግጭት ኢንዲካሄድ የፈቀደውና ያመቻቸው እርጋትና ስለማፈልግ ነው። እነዚህን ጠቃሚ መርሆዎች ማስከበር የምንችለው እኛው ነን። ይህን ለማድረግ የምንችለው በመተባበርና አብሮ በመስራት ነው።

በተጨማሪ፤ የውጭ ጠላቶችን ከበባንም ለመቋቋምና ለማጋለጥ የምንችለው እኛው ነን። ይኼን ከበባ ለመቋቋም ከቆረጥን ከሌሎች የአፍሪካ ቀንድ ጎረቤት አገሮች ተወላጆች ጋር መቀራረብና አብረን መስራት አለብን። ከበባው የሚያስጠቃው የኢትዮጵያን ሕዝብ ብቻ አይደለም። መላውን የአፍሪካን ቀንድ ተወላጆች ጭምር ነው።

ኢትዮጵያ ተብላ የምትታወቀው ሃገራችን ከተመሰረተችበት ከአራት ሽህ ዓመታት በፊት ጀምሮ የኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ፤ ዘላቂ ጥቅሞቿን ለመንጠቅ፤ ዳር ድንበሯ እንዳይከበር ለማድረግ፤ ብሄራዊ የሆነ ጠንካራና ዘመናዊ ኢኮኖሚ እንዳይመሰረት ለማድረግ ወዘተ ያልሞከሩት ተንኮል የለም። መልኩንና ዘዴውን ይቀይራል እንጅ፤ ሴራው ወደፊትም ይቀጥላል።

የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለምን ከበቧት?

ጥያቄውን ሙሉ በሙሉ ለመመለስ አልሞክርም። ቦታው አይደለም። ሆኖም፤ አራት ቁልፍና ለአገር ቀጣይነት እና እድገት ወሳኝ፤ ለውጭ ግኑነትና ለግጭት መንስኤ የሆኑ የተፈጥሮ ጥሪቶችን (Geographic as well as Natural Resources Assets) ለመጥቀስ እገደዳለሁ።

  1. የኢትዮጵያ ስትራተጂክ የጅኦግራፊ አቀማመጥ፤
  2. የኢትዮጵያ ሰፊ ለም መሬት፤ ወንዞች፤ ዝናብና ሌላ የተፈጥሮ ኃብት፤
  3. የኢትዮጵያ ረጂም ታሪክና የሕዝቧ አገር ወዳድነት፤
  4. ኢትዮጵያ በቀይ ባህር ያላት ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብት።

ባለሞያዎች ስለ አፍሪካ ሲጽፉ “የተፈጥሮ ኃብት እርግማን ነው” ይላሉ። በአብዛኛው “እርግማን” ነው። አባይን እርግማን ነው ለማለት አልችልም። የዓባይና ሌሎች ወንዞች ለኢትዮጱያ እድገት ወሳኝ ናቸው። ሆኖም፤ እንደ ዓባይ ያሉት ታላላቅ ወንዞች ወደ ኃይል ማመንጫና ወደ መስኖ ግድብ ሲቀየሩ እንደ ግብጽ ያሉትን አገሮች ስለሚያስደነግጡ አደጋዎችን መጋበዛቸው የማይቀር ነው። ለዚህ ነው በጽሁፎቸ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ኢትዮጵያዊያንን መከፋፈል የለበትም ያልኩት። አሁንም ለመደጋገግም፤ ለኢትዮጵያ ዋና ዋስትናዋ የሕዝቧ አንድነትና እድገት ነው። የተፈጥሮ ኃብት ዋና ጥቅሙ የሕዝቡን ህይወት ማሻሻሉ ነው። የጥቂቶችን ኪስ መሙላቱ አይደለም!!

በተፈጥሮ ኃብት የታወቀችው ኮንጎ ኪንሻሳ ወይንም ዛየር ነጻ ከመውጣቷ በፊትና ከወጣች በኋላ ሰላምና እርጋታ አግኝታ አታውቅም። የውጭ መንግሥታት፤ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተፈጥሮ ኃብቷን እየነጠቋት ነው። ይህች ኃብታም ለመሆን የምትችል አገር ወዳድና ዲሞክራሳዊ መንግሥት እንዳይመሰረት ከፍተኛ ሴራ ሲካሄድባት የቆየች አገር ናት። እንደ አንጎላ፤ ናይጀሪያ፤ ካሜሩን፤ ጋቦን፤ ጊኒ የመሳሰሉት ነዳጅ አምራች አገሮች በመጥፎ አስተዳደር፤ በአድልዎና በሙስና ስለተበከሉ ተራው ሕዝብ ከተፈጥሮ ኃብቱ ጥቅም አግኝቷል ለማለት አይቻልም። ይህ በአፍሪካ አገሮች የሚታየውን በመጥፎ አገዛዝ የተበከለውን አንዱን ጎን ያሳያል፤ ሌላም ጎን አለ!! ይኼ መልካም አስተዳደር ወይንም ዲሞክራሳዊ ጎን ነው።

እንደ ቦትስዋና ያሉ የመንግሥት ስርዓታቸውን ያስተካከሉ ዲሞክራሳዊ አገሮች የተፈጥሮ ኃብታቸውን ለማህበረሰባዊ አገልግሎት አውለው አስደናቂ የእድገት ውጤቶች አሳይተዋል። ከፍተኛ ገቢ አላቸው ከሚባሉት አገሮች ማካከል ቦትስዋና፤ ሞሪሺየስ፤ ሴሸልስ፤ ደቡብ አፍሪካ ይገኙበታል። ላወቀበት የተፈጥሮ ኃብት ለዘላቂና ለፍትሃዊ እድገት ወሳኝ ነው።

ሆኖም፤ የአገዛዝ ስርዓቱ አሳታፊ፤ ፍትሃዊ፤ ግልጽነትና ሃላፊነት ያለው፤ ዲሞክራሳዊ ካልሆነ የተፈጥሮ ኃብት ፋይዳ ቢስ ነው። ኢትዮጵያ ብዙ ጥሪቶች ያሏት አገር  ሆና እስካሁን የምግብ ጥገኛ የሆነችበት ዋና ምክንያት ፍትሃዊ የሆነ አገዛዝ ስለሌላት ነው።

በእኔ እምነት፤ የኢትዮጵያ ማህበረሰባዊ ጥሪቶች ከነዳጅ፤ ከእንቁና ከሌላ የበለጠ ጥቅም እንዳላቸው አምናለሁ። እኔን ያሳሰበኝ፤ ይህን እምቅ ኃብት በማባከን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን እኛው ራሳችን ተጨማሪና አጋር መሆናችን ነው። ገዢው ፓርቲ ያባክናል፤ እኛም ጥሩ አማራጭ ለመስጠት አልቻልንም። የኢትዮጵያን እምቅ ኃብትና አቅም የሚያውቁ የውጭና የአገር ውስጥ ተቀናቃኞች ኢትዮጵያ ተፈጥሮ ያበረከታትን፤ ተከታታይ ትውልድ መስዋእት ሆኖ ያቆየውን ኃብቷን ተጠቅማ ራሱን የቻለና ጠንካራ ማህበረሰብ እንዳትመሰርት ማነቆ ሆነው ቆይተዋል።  እኛም ደፍረን ይህን ተንኮል አቁሙ ለማለት አልቻልንም። ምክንያቱም ተከፋፍለናል። እርስ በርሳችን እንነታረካለን። መከፋፈላችን ለውጭ ጠላቶች አመች ሁኔታን ፈጥሯል።

ካለፈው ጥፋት እንማር

በእኔ ግምት በኢትዮጵያ ላይ ያልተጸነሰ፤ ያልታቀደ፤ ያልተቀናጀና ያልተካሄደ ሴራ (Conspiracy) የለም። በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ የውጭ ኃሎች ኢትዮጵያን ግዛታቸው ለማድረግ ሞክረው በጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ቆራጥነትና ህብረት ሴራቸው ሳይሳካ ቀርቷል። ምንም እንኳን ብዙ የሰው፤ የከብትና ሌላ የተፈጥሮ ኃብት፤ የማይተኩ የአገር ቅርሶችና ሌላ ኃብትና ጥሪት ቢያወድሙም ኢትዮጵያን ኃይል ተጠቅመው ሊገዟት አልቻሉም። ይኼ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥንካሬ ምልክት ወይንም እሴት ነው። በትሪሊየን ዶላር ሊገዛ አይችልም።

ኢትዮጵያን ለማሸነፍ መጥቶ በህይወቱ ወደ አገሩ የተመለስ የግብጽ ተወላጅ ወይንም ፈረንጅ ለማግኘት ያስቸግራል። ግብጾች ይህን ሃቅ ያውቃሉ። ለዚህ ነው የአገር ውስጥ ደጋፊዎች እየፈለጉ እኛን የሚያጠቁን። በኢትዮጵያና በግብጽ ሕዝብ መካከል ጥንታዊ የሆነ ግኑነት መኖሩን ታሪክ ይመሰክራል። የግብጽ ስልጣኔ የኢትዮጵያ በረከት መሆኑን አንርሳ!! አባይ ይባላል።

አዶልፍ ፓርለሳክ (ተርጓሚ ጆብሬ መኮንን) “የሃበሻ ጀብዱ” እና ኮ/ል አሌሃንድሮ ዴል ባዮ (ተርጓሚ ዶ/ር ተስፋየ መኮንን ባይለየኝ) “ቀይ አንበሳ” በተባሉት መጻህፍቶቻቸው እንዳስተማሩን፤ ኢትዮጵያ “ለእኔ ትገባኛለች” ብሎ ከሌሎች የአውሮፓ ቅኝ ገዢቅዎች ጋር ተመሳጥሮ ኢትዮጵያን የወረረው የጣሊያን መንግሥት በጀግናው በኢትዮጵያ ሕዝብ ብርታት፤ ህብረትና ቆራጥነት፤ በመጀመሪያ በአጼ ምኒልክ አስደናቂና ብልሃት የተሞላበት አመራር በአድዋ ተሸንፎ ያልሞተውን ወራሪ የጣሊያን መንግሥት መርከቦች ተጠቅሞ ወደ አገሩ መልሷቸዋል። በሁለተኛው ዙር የጣሊያን ወረራ የኢትዮጵያ አርበኞች ተስፋ ሳይቆርጡ አገራቸውን ከፋሽስቶች መንጋጋ ነጻ ለማውጣት ችለዋል።

ማሰብ ያለብን እንደዚህ የሚያኮራ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ ድህነትን፤ ጥገኝነትን፤ ኋላ ቀርነትንም ለማሸነፍ እነደምትችል ነው። ኦሮሞው፤ አማራው፤ ትግራዩ፤ አኟኩ፤ አፋሩ፤ ጉራጌውና ሌላው ኢትዮጵያዊ በዚህ ሊኮራ ይገባዋል!!

ህወሓቶች/ኢህአዴጎች ሲመጻደቁብን እድገትን፤ ተሃድሶን የጀመርን እኛ ነን ይሉናል። የሰው ልጆችንም “እኛ ፈጠርን” ቢሉ አያስገርምም። ሻቢያ፤ ኦነግና ህወሓት ኢትዮጵያ “የመቶ ዓመታት ታሪክ ነው ያላት” ሲሉ ነው ይህችን አገር ሊያፈርሷት ተነስተዋል ብለን መነሳት የነበረብን። ስብሃት ነጋ የትምክህተኞች ምሽግና መሰረት የሆኑትን “የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና የአማራውን ብሄረሰብ” በማያንሰራሩበት ደረጃ “አድቅቀናቸዋል” ሲል ነው አዲስ የኃይማኖት ታሪክ፤ አዲስ የኢትዮጵያ ታሪክ እንዲጻፍ ወስነዋል ብለን መረባረብና መታገል የነበረብን። ዛሬ አንዳንድ “የኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኞችና የውጭ ደጋፊዎቻቸው” ኢትዮጵያ የሚለውን ስም ፈጽሞ ለማጥፋት የተቀነባበረ ዘመቻ ይዘዋል። ኢትዮጵያን ሰርዞ “ኩሽ” ብሎ ለመሰየም፤ ለኢትዮጵያ ደጋግሞ እውቅና የሚሰጠው መጽሃፍ ቅድሱ ተቀይሮ ኩሽና ሱዳን የሚሉት እንዲተኩበት እየተደረገ ነው። እነዚህ አብዛኛውን የኦሮሞ ሕዝብ አይወክሉም።

የዛሬ ሰላሳ ዓመት ተመሳሳይ ጥረት ተደርጎ የኢትዮጵያ የክርስትና፤ የእስልምናና የሌሎች መንፈሳዊ መሪዎችና አባቶች ተሰብብሰውና ተመካክረው ይህ ሴራ ለአገሪቱና ለሁሉም ኃይማኖቶች አደገኛ ስለሆነ ለዓለም አብያተ ክርስቲያን ተቋሞችና ለሁሉም ለሚመለከታቸው ተቋሞች የሚረዳ ጠንካራ አቋም የያዘ አቋም ተወስዶ፤ የአቤቱታ ደብዳቤ ተጽፎ ይህ ወንጀል ትክክል አለመሆኑ ተረጋግጦ የተጻፉት መጻህፍቶች ሁሉ እንዳይበተኑ ተደርጎ ነበር። ከሰላሳ ዓመታት በኋላ አዲስ ምርምር፤ አዲስ የመጽሃፍ ቅዱስ ትርጉም፤ አዲስ የአገር ስያሜ እንዲካሄድ ለምን እንደ ተደረገ ሰፊ ጥናትና ውይይት በአስቸኳይ መካሄድ አለበት።

ይህ አዲስ ክስተት የገዢው ፓርቲ እጅ አለበት ወይንስ የለበትም የሚለውን ለጊዜው አልፈዋለሁ። በአጭሩ ለማለት የምገደደው ውሸት ተደጋጋሚ ሲሆን እውነት ይሆናል። እድገትን እኛ ጀመርነው የሚለው ውሸት ነው። የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመት ታሪክ ነው የሚለው ውሸት ነው።

ዘመናዊነት በህወሓት/ኢህአዴግ አልተጀመረም

አጼ ምኒልክ የአድዋ ድል መሪ ብቻ አልነበሩም። ከአጼ ቴዎድሮስ በኋላ ኢትዮጵያን በሁሉም የኢኮኖሚ ክፍሎች ዘመናዊ ለማድረግ እቅድ አውጥተው የእድገት መሰረት የጣሉት እሳቸው ናቸው። በጦርነቱ በኩል የአጼ ምኒልክ ድል ኢትዮጵያዊያንን ያስተማረን አንድ የጥቁር መንግሥት የነጭን መንግሥት በጦርነት ሲያሸንፍ ኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ መሆኗን ነው። ግን ያደረጉት ይኼ ብቻ አይደለም። የትምህርት፤ የኢንቬስትመንት፤ የሃዲድ፤ የዘመናዊ መንገድ፤ የመገናኛ ብዙሃን፤ የውጭ ግንኙነት፤ የማእደን ልማት፤ የንግድ፤ የባንክና የኢንዱስትሪ መስፋፋት ስራ የተጀመረው በእሳቸው ዘመነ መንግሥት ነው። እኛ ኢትዮጵያዊያን መሪዎች የሉንም ስንል ያሳፍራል፤ መሪዎች ነበሩን።

አጼ ቴዎድሮስ፤ አጼ ዮሃንስ፤ አጼ ምኒልክ፤ አጼ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያ ታላላቅ መሪዎች ናቸው። እነዚህ አገር ወዳድ መሪዎች እንደ ጣሊያኖች ያሉ የውጭ ጠላቶች  ኢትዮጵያን የፈለጉበትና የወረሩበት ዋና ምክንያት የራሳቸውን የስራ እድል፤ የኢኮኖሚ፤ የንግድ፤ የገበያና የተፈጥሮ ኃብት ፍላጎት ለማሟላት ነው እንጅ ለእኛ ስልጣኔን ለማምጣት አለመሆኑን ሙሉ በሙሉ ያውቁ ነበር።

ለምሳሌ ኢትዮጵያ የክርስትና ኃይማኖትን የተቀበለችና የነቢዩ ሞሃመድን እምነት ተከታዮች ተቀብላ ያስተናገደች አገር መሆኗ እየታወቀ፤ ፈረንጆች ክርስትና እንዲስፋፋ ለማድረግ የሞከሩበት ምክንያት ለምንድን ነው? እነዚህ መንግሥታት ኢትዮጵያ ዘመናዊ መሆን እንዳለባትና ዘመናዊ ለመሆን እንደምትችል ያውቁና የምኑ ነበር። ስለሆነም፤ ኢትዮጵያዊያን ከተስማማን አገራችንን ለማልማትና ዘመናዊ ለማድረግ እንችላለን። ግን መርሳት የለለብን አስኳል ጉዳይ አለ። ይኼውም፤ የአውሮፓ መንግሥታት የጣልያንን ፋሽዝም ለመቃወም ያልደፈሩበት ዋና ምክንያት አድዋን በማስታወስ ኢትዮጵያ ጣልያንን ለማሸነፍ ከቻለች እኛ ከደረስንበት ደረጃ የመድረስ እድል ሊኖራት ይችላል በሚል ግምት ይሆናል የሚል እምነት አለኝ።

 

ለእኔ የአድዋ ድል የሚያመልክተው እንደ አጼ ምኒልክ አስተዋይ፤ አገር ወዳድ፤ ሁሉን አስተናጋጅና ዘመናዊ የሆነ አመራር ያላት ኢትዮጵያን ብንመሰርት፤ ኢትዮጵያ ልክ እንደ ጃፓን፤ በአጭር ጊዜ ዘመናዊ ለመሆን ትችላለች። ለዚህ ነው፤ የአድዋ ድል ለጣሊያኖች ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ነጮች፤ በተለይ ለአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች የማይረሳ “ጥቁር ቀለም” እንደ ነበር ይታወቃል የምለው። በእኔ ግምገማ የጣሊያንና የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ሲገመግሙ “ኢትዮጵያ አሁን ባላት የኢኮኖሚና የመሳሪያ አቅም ጣሊያንን ለማሸነፍ ከቻለች ወደፊት ምን ልትሆን ትችላለች? ይህች አገር ዘመናዊ ከሆነች ከእኛ ጋር ልትወዳደር ትችል ይሆን? በአፍሪካ ቀንድ፤ በቀይ ባህር፤ በሌላው አፍሪካ ተወዳዳሪ ትሆናለች!! ኢትዮጵያ ጃፓንን ለመሆን ምን ይጎድላታል? የሚሉ ጥያቄዎችን በምስጢር እንዳስተናገዱ እገምታለሁ።

ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን ሁለተኛ ጊዜ ሲወር በአውሮፓ ተመጣጣኝ የሌለው የአየር ኃይልና ሌላ ዘመናዊ የጦር ኃይል አዘጋጅቶ ነው። ይህን ያደረገበት ዋና ምክንያት ኢትዮጵያን ለመቅበርና የተፈጥሮ ኃብቷን በበላይነት ለመቆጣጠር ነው። ትኩረት ካደረገባቸው ጉዳዮች አንዱ አገሪቱን በጎሳ ከፋፍሎ ኢትዮጵያዊነት እንዲጠፋ ማድረጉ ነበር። ገዢው ፓርቲ ከቅኝ ገዢዎች የቀዳውን “የከፈፍለህ ግዛው” ስርዓት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ጭኗል የሚባለው ለዚህ ነው።

መልኩ ይቀያይር እንጅ አሁንም ያለው የከበባ ሁኔታ ከዱሮው አይለይም። የአረብ መንግሥታት፤ በተለይ ግብጽና ሱዳን ኢትዮጵያ የአባይን ወንዝ ገድባ ለራሷ ዘመናዊነት፤ የኢንዱስትሪ ልማት፤ ብሄራዊ የምግብ ዋስትና ስኬታማነትና ለመላው ሕዝቧ የኢኮኖሚ ጥቅም ለማዋል እንዳትችል ብዙ መሳናክሎችን ፈጥረውላታል፤ እየፈጠሩላት ነው፤ ወደፊትም ይፈጥሩላታል።

አንድ አገር በእርዳታ ብቻ ዘመናዊ አይሆንም። አሜሪካኖች የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሰረት ዘመናዊ እንዲሆን ምን የረባ ነገር ሰርተዋል? ከኢትዮጵያ በገፍ የሚሰረቀውና የሚሸሸው ኃብት ወደ ራሳቸው ባንኮችና ሌሎች የኢንቬስትመንት እድል ያላቸው ቦታዎች እንዳይሄዱ ምን ጫና አድርገዋል? ለዚህ ሁሉ ተግዳሮት (Challenge) ብሄራዊ ድክመትና ውርደት መጋቢ የሆነው የራሳችን መከፋፈልና ገዢው ፓርቲ ነው።

የኢትዮጵያ ረዢም የሥልጣኔ፤ የንግድ፤ የሕዝብ እንቅስቃሴና ስርጭት፤ የኃይማኖት፤ የባህልና ሌላ ታሪክ ከባህር፤ በተለይ ከቀይ ባህር ወሰኗና ወደቧቿ ታሪክ ጋር ቀጥተኛ የሆነ ግንኙነት አለው። የኢትዮጵያ ግዛቶች ከባህር ማዶ እስከ የመንና እስከ ሳውዲ አረቢያ ይጠጉ እንደነበር የታሪክ ባለሞያዎች ያስተምሩናል። ይህ የባህር በር ባለቤትነትና ይገባኛልነት በዓረብ መንግሥታት በኩል ተቀባይነት አግኝቶ አያውቅም። ለምሳሌ፤ በአምሳዎቹ፤ በስድሳዎቹና በሰባዎቹ ዓመታት ግብጽ ኢትዮጵያ የወንዞቿንና የባህር ድንበሮቿን ባለቤትነነት አረጋግጣ የዘመናዊነት እንቅስቃሴዋን ስታካሂድ ከሌሎች የዓረብ አገሮችና በአገር ውስጥ ለመገንጠል መንቀሳቀስ ከጀመሩ ግንባሮች ጋር አብረውና ተባብረው የኢትዮጵያን የባህር በር እንዲዘጋ ለማድረግ ችለዋል። በዚህ ሴራ ተባባሪ የሆኑት ግንባር ቀደም መንግሥታት ግብጽ፤ ኢራክ፤ ሶሪያ፤ የፍልስጤም ሕዝቦች ግንባር፤ ሳውዲ አረቢያ፤ ጆርዳን፤ ሌባኖንና ሊቢያ ናቸው። እነዚህ መንግሥታት ዓላማቸውን ስኬታማ ለማድረግ የቻሉብት ዋና ዘዴ የኤርትራን ነጻ አውጭ ግንባር፤ በኋላ የኤርትራ ሕዝቦች ነጻ አውጭ ግንባር (ሻቢያ) ተብሎ ለሚጠራው የተገንጣይ ቡድን ያልተቆጠበ የዲፕሎማሲ፤ የመረጃ፤ የመሳሪያ፤ የገንዘብ፤ የመሸሸጊያና ሌላ ድጋፍ በመስጠት ነው።

October 5,2017

 

 

 

በኢትዮጵያ ላይ ያንዣበበውን የውጭ ኃይሎች ሴራ እንዴት ለመቋቋም እንችላለን? – አክሎግ ቢራራ (ዶር)